“THE PHILOSOPHY OF FOOTBALL፡ UNDER THE SHADOWS OF MARCELO BIELSA” ለአራት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተደረገበት ሥራ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙረያ ቡና ፉት እየተባለ ከተደረጉ ምሁራዊ ውይይቶች አንስቶ ማርሴሎ ቢዬልሳን የተመለከቱ በርካታ ቃለ-መጠይቆችን መሥራት ጠይቋል፡፡ የእግርኳስ ሐሳባውያኑን ፍለጋ የተደረጉ የውጭ ጉዞዎችና አያሌ መጻሕፍትን መዳሰስም የዚህ መጽሐፍ ግብዓቶች ሆነዋል፡፡ ጸሃፊው በዚህኛው ምዕራፍ አርጀንቲናዊው የእግርኳስ ታክቲክ ባለሟል ከሌሎች በተለየ ኅልዮታዊ ልህቀት ያገኙበትን ምስጢራት ለማብራራት ይጥራል፡፡
በማርሴሎ ቢዬልሳ ቤተ-ዕውቀት ውስጥ ከሌሎች የበለጠ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሉዊ ቫን ሃል ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ ቫን ሃል በቅርብ ዘመናት የዓለም ትልልቅ የእግርኳስ ክለቦች በሆኑት ባየር ሙኒክ፣ ባርሴሎና፣ አያክስና ማንችስተር ዩናይትድ አሰልጥነዋል፡፡ ከአሰልጣኙ የቀደመ የአጨዋወት ምርጫ አንጻር የሚወደድ አቀራረብ እንዳልነበረው ብዙ የተወራለትና በ2014ቱ የብራዚሉ ዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ያገኘውን የሆላንድ ብሄራዊ ቡድንም መርተዋል፡፡ ከማንችስተር ዩናይትድ ውጪ ቫን ሃል ትልልቅ ቡድኖችን ለሃገር ውስጥና ለዓለምአቀፍ ድሎች በማብቃት ተክነዋል፡፡ በአያክስ ቆይታቸው ልምድ በሌላቸው ወጣቶች ያዋቀሩትን ቡድን ለተከታታይ የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ አድርሰው በአንዱ ድል አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ አንጸባራቂ ስኬቶች በኋላ ቫን ሃል በ2009 የአልክማር ከተማ ክለብ የሆነውን ኤ.ዚ.አልማርን ለማሰልጠን ተስማሙ፡፡ በዚሁ ዓመት ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ እንኳ የሚከብደውን የኤሬዲቪዚዬ ዋንጫ ወደ ትንሹ ክለብ አመጡ፡፡ ይህን ታሪካዊ ድል ለማሳካት አያክስን፣ አይንድሆቨንን፣ ፌይኖርድንና ኤፍ.ሲ.ትዌንቴን የመሳሰሉ የሃገሪቱ ኃያላን ክለቦችን ጫና መቋቋም ነበረባቸው፡፡
በ1995 በአያክስ እና በጣልያኑ የወቅቱ ታላቅ ቡድን ኤሲ ሚላን መካከል የተካሄደውን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ማርሴሎ ቢየልሳ ደግመው-ደጋግመው አይተውታል፤ በዘላቂነት የሚያዩትም ይመስለኛል፡፡ ይህን ስለማድረጋቸው እርግጠኝነት ይሰማኛል፡፡ በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ታሪክ አራት የፍጻሜ ጨዋታዎች ባስተናገደው የኧርነስት ሃፔል ስታዲየም የሉዊ ቫንሃል አያክስ ያሳየው የአጨዋወት ዘይቤ እና ማርሴሎ ቢዬልሳ በቅርብ ዓመታት በቺሊ ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም በአትሌቲክ ቢልባኦ ክለብ ቆይታቸው በፎርሜሽኖች ላይ እንዲኖር የሚሹት ዋላይነት እንዲሁም ፍሰቱን የጠበቀ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ ቦታ አያያዝ ላይ ያላቸው አቋም ማራኪነት ተመሳስሎ አለው፡፡
ከጊዜያት በኋላ በቢዬልሳ ተቀባይነት ያገኘው ሐሳብ ቀድሞ በአያክሶች በተግባር የታየ ነበር፡፡ ኤድጋር ዳቪድስ እና ሮናልድ ደቦር በ1-3-3-3-1 ፎርሜሽን መሃል ሜዳ ላይ ከፍራንክ ራይካርድ ፊት በመሐል አማካይነት እንደሚሰለፉ ይጠበቅ ነበር፡፡ እዚህ ላይ በፎርሜሽኖች አሰያየም የግብ ጠባቂውን መስመር መጥቀስ የግድ ይላል፡፡ በሶሥት የመሃል ተከላካዮች የተዋቀረው የአያክሶች የኋላ ክፍል ፍራንክ ደቦር፣ ማይክል ሬይዚገርንና ዳኒ ብሊንድን አካቷል፡፡ ከዚህ የተከላካይ መስመር ሁለቱ መደበኛ የመሃል ተከላካዮች ሲሆኑ አንደኛው ግን የጠራጊነት ሚና የሚወጣ ተከላካይ ነበር፡፡ ይህ የተከላካይ ክፍል በከፍተኛ መግባባት ላይ ተመስርቶ ጠንካራ ጥምረት በመፍጠር በጨዋታ ወቅት የሜዳውን ስፋት የማጥበብ ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣ ዘንድ ሁሌም ይጠበቅበት ነበር፡፡
በመከላከል የጨዋታ ሒደት ወቅት የመስመር አማካዮች ወይም በሜዳው ስፋት የሚጫወቱ አማካዮች ወደኋላ እየተመለሱ በሶስት የመሃል ተከላካዮች እና በግራና ቀኝ የሜዳው ቁመት መስመሮች መካከል የሚኖረውን ጥልቅ ክፍተት የመሸፈን ኃላፊነት እንዲወጡ ማሰብ አዲስ አይደለም፤ ቀድሞም ሲተገበር የሰነበተ አጨዋወት ነው፡፡ በሌላ ሁኔታ ከሁለቱ የመስመር አማካዮች አንደኛው ወደኋላ ሲያፈገፍግ በሦስት ተከላካዮች የተዋቀረው የተከላካይ ክፍል የአደረጃጀት መዋቅሩን ሳያዛንፍ ያለምንም እንከን ወደ ሌላኛው መስመር ይጠጋል፡፡ ይህም በአራት ተጫዋቾች የሚከላከል ክፍል ይፈጥራል፡፡ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ በዊጋን ቆይታቸው ይህንኑ ታክቲካዊ ሽግሽግ ከተጫዋቾቻቸው ይጠብቁ ነበር፡፡ ለዚህኛው የመከላከል ሽግግር ሉዊስ ቫን ሃል የፈጠሩት ስልት የተለየ ነው፡፡ ሁለቱ የመሃል አማካዮች (ዳቪድስ እና ደቦር) ወደኋላ በማፈግፈግ የተጋጣሚ ቡድን የመስመር አማካዮችን እግር በእግር እየተከታተሉ የመከላከል አደረጃጀቱ አካል ይሆናሉ፡፡ ይህኛው ስልት በሶስቱ የመሃል ተከላካዮች የእርስ በእርስ እንቅስቃሴያዊ አደረጃጀት መካከል የመለጠጥ ችግር እንዳይከሰት ያግዛል፡፡ ጥበቱን እንደጠበቁ እንዲጫወቱም ይረዳቸዋል፡፡
ይህ የቫንሃል የተከላካይ ክፍል አጨዋወት እስከዛሬም ድረስ ልዩ እና ለመተግበር ቀላል ሆኖ የተገኘው በበቂ ምክንያት ነው፡፡ ከሶሥቱ አማካዮች ሁለቱ የመሃለኛው ሜዳ ቦታቸውን ለቀው ወደኋላ ስለሚሄዱ መሃሉ ክፍል ላይ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ከዚህኛው ወሳኝ የሜዳ ክልል ተጋጣሚን በአንድ ተጫዋች ብቻ የመጋፈጥ አደጋ ያስከትላል፡፡ በርካታ የግብ ዕድሎች የሚመነጩት ከየትኛውም ቡድን አማካይ ክፍል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሉዊስ ቫን ሃል በ10-ቁጥር ሚና በአጥቂ አማካይነት የሚሰለፈውን ያሪ ሊትማነን ወደኋላ አፈግፍጎ ከፍራንክ ራይካርድ ጎን እንዲጫወት በማድረግ በመከላከል የጨዋታ ሒደት አያክሶች በጥምር ተጫዋቾች የሚመራ የአማካይ ክፍል እንዲኖራቸው አደረጉ፡፡
ከ1-3-3-3-1 ወደ 1-5-4-1፣ ከመሃል አማካይነት ወደ መስመር ተከላካይነት፣ ከተለምዷዊ አሰላለፍ ወደ አዲስ ሚና…
ምስል፦ ከሚላን ጋር በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ የአያክስ የማጥቃት ፎርሜሽን (ግንቦት 24-1995)
ምስል፦ ከሚላን ጋር በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ የአያክስ የመከላከል ፎርሜሽን (በግንቦት 24-1995)
በጨዋታ ወቅት ብዙ እንቅስቃሴ ይደረግበታል ተብሎ የሚታሰበውን የተወሰነ የሜዳ ክፍል (Position-Slot) መለዋወጥ በራሱ ቀልብ የሚስብ ሐሳብ ነው፡፡ ይህንን እግርኳሳዊ ሐሳብ እኔ ራሴ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቤቱ ዋና አሰልጣኝ ሳለሁ በሥራ ላይ አውዬዋለሁ፡፡ ለዚህ መጽሃፍ ግብዓት ይሆኑኝ ዘንድ ከተለያዩ ጉዞዎቼ የሰበሰብኳቸው መረጃዎች በዋና አሰልጣኝነት በተሳተፍኩበት ሥራ ለአንድ ዓላማ የሚቆም ቡድን ከመሥራት የሚገኘውን ትምህርት ይበልጥ ግልጽ አድርጎልኛል፡፡ ይህ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ቡድን አሰልጣኝነት ተመክሮዬ ብዙዎች በእግርኳስ ሊያገኙ የማይችሉትን አዳዲስ ሐሳቦችን በተግባር ለመሞከርና ለመፈላሰፍ እድል ሰጥቶኛል፡፡ ሁኔታዎች አመቻችቶልኛል፡፡ ከሁሉም በላይ እግርኳስ የምመለከትበትን አተያይ እንድቀይር እና በሐሳብ እምነት ስለማሳደር እንዳስብ ትምህርት ሆኖኛል፡፡
ከማንም ሰው በላይ የማርሴሎ ቢዬልሳ መሰረታዊ ሐሳቦችና የዕምነት መርሆዎች የዚህን መጽሃፍ ፍሬ ነገሮች ለማጠናቀር ረድቶኛል፡፡ ይሁን እንጂ መጽሃፉ በአሰልጣኙ ፍልስፍና ዙሪያ ያጠነጠነ የግል አረዳዴ ትርጉም በመሆኑ በውስጡ የሚቀርቡት ናሙናዎች በሙሉ በእኔ ልምድ በተሻለ ያወቅኋቸው አልያም በቅርብ የተረዳኋቸው
ናቸው፡፡ ከቢዬልሳ ጋር ከሰሩ ሰዎች ጎን ተቀምጬ ለማውጋት ብዙ ሃገራትን ዞሬያለሁ፤ ከእርሱ ሥር በተጫዋችነትም ሆነ በረዳትነት ያሳለፉ ባለሙያዎችን ፍለጋ ያላዳረስኩት ቦታ የለም፡፡ በእርሱ ዙሪያ ወይም በአጋዥነት አብረው ያሳለፉ ዕድለኞችን በየስፍራው ላገኝ ጥሬያለሁ፡፡ በሃሜትና በጭምጭምታ ወሬ የአርጀንቲናዊውን ስም በክፉ ለማንሳት ከማይወዱ ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ስለ ንጹህ የእግርኳስ አጨዋወት አውርቻለሁ፤ የእርሱን የጨዋታ ሥልት ከጥቅም ውጪ ስለሚያደርግ ታክቲካዊ መፍትሄም ብዙ ሰምቻለሁ፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከራሴ የሆነ አዲስ ያበረከትኩት ሐሳባዊ አስተዋጽኦ እንደሌለኝ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በውስጡ ከቀረቡ አስገራሚ የአጨዋወት ሐሳቦች ውስጥ አንዳቸውም የእኔ አይደሉም፡፡ ተመሳሳይ ዕምነት ካላቸው በርካታ ታላላቅ አሰልጣኞች የተለያዩ ሐሳቦችን ወስጄ አንድ ላይ ከማሰባሰብ ባለፈ ያደረግሁት የተለየ ነገር የለም፡፡ መጽሃፉን ለማዘጋጀት በተደረገው ጥረት ሐሳቦቹን በጥልቀት የመረዳትና ወሰውሰብ ያሉትንም ለመፍታት የሚያስችል ከፍተኛ ልምድ የማግኘት አጋጣሚ ፈጥሮልኛል፡፡
” እኔ ስለ ራሴ ብቸኛ ህላዌነት እርግጠኛ ስሜት አይሰማኝም፤ ይልቁንም እኔ ያነበብኳቸው ደራሲዎች፣ ያገኘኋቸው ሰዎች፣ በፍቅራቸው የከነፍኩላቸው እንስቶች፣ የጎበኘኋቸው ከተሞች፣…ውጤት ነኝ፡፡” – ሆርሄ ሉዊስ ቦርሄስ
ሁሌም በቢዬልሳ ታክቲካዊ አስተሳሰብ ዙሪያ የሚደረጉት እግርኳሳዊ ውይይቶች በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንዲጠናቀሩ ይደረጋል፡፡ ይህ መጽሐፍ ትኩረቱን ለውይይት በሚቀርቡት ሐሳቦች ዙሪያ እንጂ በተወያዮቹ ማንነት ላይ አያደርግም፡፡
መጽሃፉ እግርኳስ እና እግርኳስ ላይ ብቻ ያጠነጥናል፤ የሐሳባውያኑን ግለሰባዊ የአደባባይ ስብዕናን መዳሰስ የመጽሃፉ ዓላማ አይደለም፡፡ ይህ መጽሐፍ ከሌሎች ሥራዎች የበለጠ በህይወቴ ተፈላጊ እንደሚሆን እና የታለመለትን ግብ እንደሚመታ እምነቴ ነው፡፡ አንባቢዎችም በመጽሃፉ ውስጥ የተካተቱትን እግርኳሳዊ ሐሳቦችና መመሪያዎች ላትቀበሏቸው ትችሉ ይሆናል፡፡ በተጻራሪ ሁኔታ እግርኳስን የምታዩበትን መነጽር በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሮባችሁ በማርሴሎ ቢዬልሳ ፍልስፍና ማዕቀፍ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች ሊገለጥላችሁም ይችላል፡፡ የቢየልሳ ተከታዮች በሆኑት ታማኝ ደቀመዛሙርቱ ፔፕ ጓርዲዮላ፣ ማውሪዚዮ ፖቼቲኖ፣ ሄራርዶ ማርቲኖ፣ ሆርሄ ሳምፓውሊ፣ ኤድዋርዶ ቤሪዞ፣…በተጓዙበት የሐሳብ ፈለግ እናመራም ይሆናል፡፡ ያኔ እኔም እናንተም “ቢየልሲስታ” ሆንን ማለት ነው፡፡
ይቀጥላል…
የመጽሃፉ ደራሲ ጄድ ሳይናን ዴቪስ ይባላል፡፡ ዌልሳዊው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዋና አሰልጣኝነት፣ በኢስቶኒያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት በአሁኑ ወቅት <ኦታዋ ፈሪ> በተባለው የካናዳ ክለብ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከ2019 ጀምሮ በኦታዋ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የእግርኳስ ፕሮፌሰር ሆኖ Strategy in Association Football ያስተምራል፡፡ ዴቪስ በ2013 ” Coaching the Tiki-Taka Style of Play” የተሰኘ መጽሃፍ አሳትሟል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ