ይህን ያውቁ ኖሯል? (፭) | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ…

በዛሬው ይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የተመለከቱ ዕውነታዎችን እያቀረብን እንገኛለን። ለዛሬ ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫን የተመለከቱ ዕውነታዎች ይዘን ቀርበናል።

– ኢትዮጵያ ከ32 የአፍሪካ ዋንጫዎች በአስር ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ ከነዚህ አስር ውድድሮች መካከል በማጣርያ ያለፈችው በአራት አጋጣሚዎች (1957፣ 1962፣ 1974 እና 2005) ብቻ ነው። ሦስት ጊዜ በአስተናጋጅነት፣ አንድ ጊዜ ባለፈው ቻምፒዮንነት እንዲሁም የመጀመርያዎቹ ሁለት ውድድሮችን ደግሞ የተሳታፊ ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ውድድሩ አምርታለች።

– ኢትዮጵያ መሳተፍ ከነበረባት 26 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድሮች መካከል በ22 ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። በሁለት አጋጣሚዎች (1978 እና 1992) አስቀድማ ራሷን ስታገል አንድ ጊዜ (1988) ከታንዛንያ ጋር የመጀመርያ ጨዋታ አድርጋ የመልሱን ጨዋታ ሳታደርግ ራሷን አግልላለች። አንድ ጊዜ ደግሞ (2002) የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎችን እያከናወነች ባለችበት ወቅት በፊፋ በመታገዷ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

– ዋልያዎቹ ከተሳተፉባቸው 22 የማጣርያ ውድድሮች በአራቱ (1957፣ 1962፣ 1974 እና 2005) ስኬታማ ሆነው ወደ ውድድሩ ሲያልፉ ያለፉት መንገድም የሚከተለው ነው።

1957 – በምስራቅ አፍሪካ ዞን የዙር ጨዋታ ከአራት ቡድኖች ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ አልፋለች።
1962 – ከታንዛንያ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ብቻ አድርጋ በድምር ውጤት አልፋለች።
1974 – በቅድመ ማጣርያ (ሩዋንዳ) እና አንደኛ ዙር (ጊኒ) በደርሶ መልስ በማሸነፍ አልፋለች።
2005 – በመጀመርያ ዙር (ቤኒን) እና በሁለተኛ ዙር (ሱዳን) አሸንፋ አልፋለች።

– ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው 22 የማጣርያ ውድድር መካከል አራት ጊዜ ከቅድመ ማጣርያ ስትሰናበት ሦስት ጊዜ ከአንደኛ ዙር፣ አንድ ጊዜ ከሁለተኛ ዙር ተሰናብታለች። በ10 ውድድር ከምድብ ስትሰናበት በቀሪው አራት ውድድር ደግሞ ወደ ዋናው ውድድር አልፋለች።

– በማጣርያ ውድድር ኢትዮጵያ በሰፊ ጎል ያሸነፈችው ጨዋታ በ1970 የሱዳን አፍሪካ ዋንጫ (በኢትዮጵያ 1962) ማጣርያ ሲሆን ታንዛኒያን 7-0 የረታችበት ነው።

– በተቃራኒው በሰፊ ጎል የተሸነፈችበት ጨዋታ የተመዘገበው በ1998 የቡርኪና ፋሶ አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ (በኢትዮጵያ 1990) በግብፅ ያስተናገደችው የ8-1 ሽንፈት ነው።

– የምድብ ማጣርያ መደረግ ከጀመረበት የ1992 አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ (በኢትዮጵያ 1984) ወዲህ ኢትዮጵያ ከምድብ አልፋ ወደ አፍሪካ ዋንጫው አምርታ አታውቅም። ሆኖም ከዛ ወዲህ በአንድ አጋጣሚ (2005) ፎርማቱ ተቀይሮ በሁለት ጨዋታ ብቻ አላፊዎች ሲለዩ ማለፍ ችላለች።

– የምድብ ማጣርያ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ለ2017 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2009) ውድድር ማጣርያ ሁለተኛ የጨረሰችበት ነው። በወቅቱ ከአልጄርያ አንሳ ሲሸልስ እና ሌሶቶን በልጣ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!