ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አሰልጣኙን በይፋ አስተዋውቋል

ዛሬ በሸራተን ሆቴል በተከናወነ ሥነ-ስርዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ የአሰልጣኝ  ኤርነስት ሚደንዶርፕን ቅጥር ይፋ አድርጓል።

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ኤርነስት ሚደንዶርፕን ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ የቅዱስ ጊዮርጊስን ዋና አሰልጣኝነት ቦታ እንደሚረከቡ መገለፁ ይታወሳል። ከዚህ ቀድም 20 የሚደርሱ ክለቦችን ያሠለጠኑት እኚህ አሰልጣኝ በሀገራቸው ክለቦች ዋናነት በአርሜኒያ ቤለፊልድ ፣ ቦኸም እና ኦግስበርግ፣ በጋናዎቹ አሻንቴ ኮቶኮ እና ኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካዎቹ ጎልደን አሮውስ፣ ካይዘር ቺፉስ እና ማርትዝበርግ ዩናይትድ አሳልፈዋል። አሁን ደግሞ የሪከርድ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኖቹን ለመያዝ ከተስማሙ በኋላ ዛሬ ረፋድ በሸራተን አዲስ በተከናወነ ሥነ-ስርዓት የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዘዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል እና ዋና ፀሀፊው አቶ ንዋይ በየነ በተገኙበት በይፋ ተዋውቀዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ ከተጫዋቾቻቸው ጋር ለመግባባት አማርኛ ቋንቋን ለመረዳት እንደሚሞክሩ በመግልፅ ፈገግ በሚያስብል አስተያየት ሀሳባቸውን መግለፅ የጀመሩት አሰልጣኙ ከጀርመን ውጪ በአፍሪካ የጋናውን አሻንቲ ኮቶኮን በማሰልጠን ወደ አህጉራችን እንደመጡ አንስተው በጋና እና በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው የአፍሪካን እግር ኳስ የማወቅ ዕድል እንዳገኙ አስረድተዋል። እንደሰጡት አስተያየትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣውን ጥያቄ ተቀብለው ስለክለቡ ለመረዳት እምብዛም ጊዜ ያልወሰደባቸው አሰልጣኝ ሚደንዶርፕ ክለቡ ለቻምፒዮንነት እንደሚጫወት እና በቀረው አጭር ጊዜ ቡድኑን አዘጋጅቶ ህልሙን እውን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መረዳታቸውን ገልፀዋል።

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ” ከባድ ኃላፊነት ቢሆንም በተለያዩ ሀገራት ክለቦች ባካበትኩት ሰፊ ልምድ ባለው የተጨዋቾች ግብዓት በፍጥነት ቡድኑን እሰራለሁ። ” የሚል አስተያየታቸውን ሰንዝረው የሚመርጡትን የአጨዋወት ዘይቤ በአመዛኙ የቡድኑን ተጫዋቾች ጠንካራ ጎኖች ከገመገሙ በኋላ እንደሚወስኑ ጠቁመዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስን የዓምና የተወሰኑ ጨዋታዎችን እንዲሁም የትናንቱን የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታ የተመለከቱ ሲሆን በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ጨዋታ አድናቂ ቢሆኑም በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት ሄዶ ግብ ማስቆጠርም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በአስተያየታቸው አንስተዋል።

በመቀጠል የአሰልጣኙን ቅጥር እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት የክለቡ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል በበኩላቸው ይህን ብለዋል። “እስካሁን ብዙ አሰልጣኞች መጥተው ሄደዋል። ከዚህ ቀደም ከመጡት ጋር ስናነፃፅራቸው የአሁኑ አሰልጣኛችን በሙያቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ እና በአፍሪካ የተለያዩ ክለቦችን በአህጉራዊ ውድድሮች በከፍተኛ ደረጃ ያሰለጠኑ ናቸው። ኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን ገብቶ ውድድሮች በተቋረጡበት ወቅት የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ለዚህ ዓመት መዘጋጀት ከጀመርን ስምንት ወር ይሆነናል። ” ብለዋል።

እንደ ሊቀመንበሩ ሀሳብ ‘ለውጥ ለማምጣት እስከመጨረሻው መጓዝ አለብን’ በሚል ታጥቀው በመነሳት ከፍ ያለ ዋጋ በመክፈል አሰልጣኙን ማምጣታቸውን ተናግረው የዘንድሮው ውድድር የቴሌቪዢን ሽፋን ከማግኘቱ ጋር እንዲሁም 85ኛውን የክለቡን ልደት ከማክበር ጋር በተገናኘ ቡድኑ ዓመቱን በድል ለመጨረስ በሁለም ረገድ ዝግጁ ሆኖ ለመቅረብ እንዲረዳው ሲሰሩ እንደቆዩ ገልፀዋል። ንግግራቸውን ሲያገባድዱም ይህን ስራ ለማሳካት አብረዋቸው የለፉ ባልደረቦቻቸውን አመስግነዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ማብቂያ ላይ አሰልጣኙ የክለቡን መለያ ይዘው ከአመራሮቹ ጋር ፎቶ በመነሳት በይፋ ቡድኑን መረከባቸው ከመመልከቱ በፊት ሦስቱ ግለሰቦች ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። በአንኳርነት ያነሷቸውን ሀሳቦችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አሰልጣኝ ኤርነስት ሚደንዶርፕ

ከገንዘብ በላይ ከክለቡ አመራሮች ጋር ስነጋገር እና ክለቡ ባለፉት አሰልጣኞች በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ያደረገውን ተሳትፎ ስመዝነው በአህጉራዊ ውድድር ላይ ተፎካካሪ ሆኖ የመቅረቡ ፕሮጀክት የሚሳካ መስሎ ስለተሰማኝ ነው ሥራውን ለመውሰድ የተስማማሁት።

ይህን ነገር ለመሥራት ነው የምፈልገው ብሎ ከለብ መያዝ ከባድ ነው። እንደሚኖሩት ተጫዋቾች እና እንደሁኔታው ተለዋዋጭ የሆኑ አጨዋወቶችን ለመተግበር ፍቃደኛ መሆን እና ቡድኑን ሜዳ ላይ ለተለያዩ አጨዋወቶች እንዲሆን አድርጎ መገንባትን ይበልጥ አምንበታለሁ። ደረጃ በደረጃ ዕድገቱን የጠበቀ ግን ደግሞ በፍጥነት ጥሩ ቡድን መስራት ላይ አተኩራለሁ።

መድረሻችን ግልፅ ነው። ገና በዝርዝር ባንነጋገርበትም እንደ ጊዮርጊስ ላለ ክለብ በአዲስ የውድድር ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆን ዋነኛ ዓላምው ነው። ይህን ለማሳካት ከአሰልጣኞች ቡድኑ ጋር በሮትጋት የምንሰራ ይሆናል። ክለቡም ሆነ ደጋፊው ዋነኛ ፍላጎታቸው ይህ ይመስለኛል።



አቶ አብነት ገብረመስቀል

ከዚህ በፊት ተጫዋች እና አሰልጣኝ ስንመርጥ ውድድር ወይም ዝግጅት ከጀመርን በኋላ ነበር። ያ ችግር እየፈጠረ በመምጣቱ እና በ ኮቪድ 19 ምክንያትም ሰፊ ጊዜ ስለነበርን አሰልጣኙን በሰዓቱቶ አምጥተናል። ሀገሪቷ ውስጥ የሚሸጥ ብዙ ተጫዋች የለም። ይሉት የታወቁ ናቸው። ካሉት ውስጥም የሚጠቅመንን ባሉን ክፍት ቦታዎች ላይ አስፈርመናል።

የአሰልጣኙ መምጣት ክለቡን እና የአሰልጣኞች ቡድኑን ብቻ ሳይሆን አካዳሚውንም የሚነካ ነው። የቴክኒክ ሰው ስለሆኑ አካዳሚም ላይ ትልቅ ዕገዛ እአድርገውልን እንደምንጀምረው ተስፋ ሰጥተውናል።

ክለባችን የህክምና ቡድን አለው። ከስፖርት ህክምና ክሊኒክ ጋር ኮንትራክት ገብተናል። ተጫዋቾች ከሆስፒታል ሆስፒታል የሚንከራተቱበት ሁኔታ አይኖርም

ለእዚህ ሀገር ውድድር የውጪ አሰልጣኝ አያስፈልገውም። ልጆቹ ራሳቸው ገብተው የሚያሸንፉበት ዓይነት ውድድር ነው። ነገር ግን እኛ አላማችን አፍሪካ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪኩ አንድ ቦታ ላይ ደርሶ የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራት ነው።

ክለባችን ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉትን ተጫዋቾች ሰብስቦ ይዟል። የውጪዎቹን ደግሞ አሰልጣኙ አይተው የሚጨምሩ ይሆናል።

አቶ ነዋይ በየነ

እስከዛሬ ከምናመጣቸው አሰልጣኞች በልምድም ይሁን በሲቪያቸው ከፍ ይሉ አሰልጣኝ አምጥተናል። ከእንደዚህ ዓይነት አሰልጣኞች የሜዳ ላይ ውጤት ብቻ ሳይሄን አስተዳደርንም ነው የምንማረው። ከስልጠና አንስቶ በሁሉም መንገድ የቡድኑን አደረጃጀት በማሳደግ ወደ ትልልቆቹ ክለቦች ደረጃ ያደርሱናል በሚል ነው አሰልጣኞችን የምንቀጥረው።

እንዲህ ዓይነት አሰልጣኝ ማምጣት የገንዘብ ጉዳይ ብቻ ሳይሄን የሊግም ጉዳይ ጭምር ነው። ጉዳዩን ከባድ አድርጎብንም የነበረው የሊጉ ደረጃ ምን አይነት ነው የሚለው ጥያቄ ነበር።

ባለለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት የቁልቁለት ጉዞ ነበር የያዝነው። አሁን ጉዳዩ ይስተካከላል የሚል ዕምነት አለን። ክለቦች ፊትለፊት እርስ በእርስ በሚላቀቁበት ሊግ ውስጥ መውዳደር እጅግ በጣም ይከብዳል። ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ውድቀቱ የጋራ ነው ብሎ አምኖበት እንዲሄድ ያልተቋረጠ ትግል ያስፈልጋል። የአንድ ውድድር ባለዋንጫ መሆን ብቻውን ምንም ግብ ሊሆን እንደማይችል በቂ ማስረጃዎች አሉ። እነደዚህ ዓይነት ባለሙያዎችን ወደ ሊጋችን ስናመጣ ይህን ሁሉ ኃላፊነት ተሸክመን ነው።

እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አይነት ወይም ማንኛውም የሊጉ ክለብ እየፈረሰ የሚሰራ መሆን የለበትም። ክለቦች ለየቦታው የሚመጥን ተጫዋች የመመልመል አደረጃጀት ሊኖራቸው ይገባል። አንድ አሰልጣኝ ሲመጣ ሀያ እና ሰላሳ ተጫዋች እያመጣ የሚሰራው ቡድን ሊኖረን አይችልም። ያሉትን ክፍተቶች የመሙላት ኃላፊነት የአስተዳደሩ ነው።

እኚህ አሰልጣኝ ሲመጡ የሰባት ወይም የስምንት ሳምንት ጊዜ አለ። በምንም መለኪያ አልዘገየንም። ማንንም አሰልጣኝ ብናመጣ እና ኮቪድ ባይኖር ውድድሩ ይሄኔ ተጀምሮ ነበር። በሁለት እና ለሦስት ሳምንት ውስጥ ነበር ውድድር ውስጥ የምንገባው። በውድድር መሀልም አሰልጣኝ ይቀየራል። የአሰልጣኙ ብቃት ፣ የተጫዋቾቾቹ ፍቃደኝነት እና የአመራሩ ቁርጠኝነት ነው የሚወስነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመርህ ነው አሰልጣኝ የሚቀጥረው። ማንም አሰልጣኝ የገባውን ውል ካልፈፀመ እናባርራለን። ይሄ ጣልቃ ገብነት አይደለም። ጣልቃ ገብነት በአሰላለፍ እና በልምምድ ጉዳዮች ውስጥ ስንገባ ነው። አሰልጣኙ የሚፈልገውን ሁሉ እናሟላለን። ከዛ ውጪ ግን ጣልቃ መግባት በታሪካችን ውስጥ ኖሮ አያውቅም

ይሄን ያህል መስዕዋትነት የከፈልንባቸውን አሰልጣኝ ጣልቃ በመግባት የሚፈልጉትን እንዳይተገብሩ ካደረግን ከፍተኛ የዋህነት ነው የሙሆነው። ከዛ ውጪ ዘንድሮ ቡድኑን የኢትዮጵያ ቻምፒዮን ማድረግ ይኖርባቸዋል። በሚቀጥሉት ዓመታት ግን በፊትም እንደምናስቀምጠው በቻምፒየንስ ሊጉ የመጨረሻ ስምንት ውስጥ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ደግሞ ለዋንጫ የመድረስ ኃላፊነት ይኖራቸዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!