የኒጀር እና የኢትዮጵያን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

ኅዳር 4 በኒያሜው ስታድ ጀነራል ሴኒ ኮንቼ ስታዲየም ላይ የሚደረገውን የኒጀር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታን የላይቤሪያ ዜግነት ያላቸው ዳኞች ይመሩታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ልምምዱን አዲስ አበባ በሚገኘው የካፍ አካዳሚ እየሰራ ቀናቶችን አስቆጥሯል፡፡ ቡድኑ ከልምምድ ባለፈም በወዳጅነት ጨዋታ ባለፈው ሐሙስ ከዛምቢያ አቻው ጋር የተገናኛ ሲሆን በነገው ዕለትም በአዲስ አበባ ስታዲየም ዛምቢያን በድጋሚ ይገጥማል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ልምምዱን እዚሁ አዲስ አበባ ላይ ካከናወነ በኃላ ህዳር አራት ላይ ኒጀርን ይገጥማል። ካፍ ትላንት ምሽት ይፋ እንዳደረገው ከሆነም ይህን ጨዋታ አራት የላይቤሪያ ዜግነት ያላቸው ኢንተርናሽናል ዳኞች ይመሩታል፡፡ የ29 ዓመቱ ሀሰን ዚናህ ኮርኔ በዋና ዳኝነት ጨዋታውን ሲመሩት ሴኮህ ካኒ እና ዩኤል ዎንካ ረዳቶቹ ፣ ጆርጅ ሩጀርስ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል፡፡ የብሩኪናፋሶ ዜግነት ያላቸው ያሜኦጎ ኮኦዶጉ ደግሞ የጨዋታው ኮሚሽነር ሆነዋል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በሦስተኛው ዙር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የልተመደቡ ሲሆን በአንፃሩ ሠለሞን ገብረስላሴ ናይጄሪያ ከሴራሊዮን የሚያደርጉትን ጨዋታ ይታዘባሉ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!