የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪው አርባምንጭ ከተማ የአሰልጣኝ ጌታነህ ኃይሉን ውል ሲያራዝም አንጋፋዋን አጥቂ አስፈርሟል፡፡
ከ2011 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ላይ ተወዳዳሪ የሆነው እና አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን እያፈራ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ለ2013 የውድድር ዓመት ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ ንጉሴ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከሌሎች ክለቦች ከማስፈረም ይልቅ ተስፈኛ እና ዕድሉን ማግኘት አለባቸው ብለው ያሰቧቸውን የሙከራ ዕድል በመስጠት ተመልክተው ጥሩ አቅም ያሳዩትን እንደሚያስፈርሙ የነገሩን ሲሆን ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ግን በጥቂቱ ወደ ስብስባቸው እንደሚያካቱም ጭምር ገልፀውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የቀድሞዋ የደደቢት እና የንግድ ባንክ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ከእግር ኳሱ ራቅ ብላ የነቀረችው አጥቂዋ ሰናይት ባሩዳ በአንድ ዓመት ውል አርባምንጭ ከተማን የተቀላቀለች የመጀመሪያዋ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ሆናለች፡፡
ክለቡ በተጨማሪም ያለፉትን አምስት ዓመታት ቡድኑን በአሰልጣኝነት ሲመራ የነበረው ጌታነህ ኃይሉ (ቡቂቻ) ዘንድሮ በክለቡ እንዲቀጥል ውሉን አድሶለታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!