ከዚህ ቀደም ከተለመደው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት በተለየ መልኩ ይከናውናል የተባለለት መርሐ-ግብር በቴሌቪዢን እንደሚተላለፍ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አ/ማ ባስቀመጠው የውድድር ፕሮቶኮል መሠረት ለክለቦች ቅድሚያ ትዕዛዝን ካስተላለፈ በኃላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታኅሣሥ 3 እንደሚጀመር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ሊጉ ካለፉት ዓመታት በተለየ ተመልካች በማይገኝበት እና በቀጣዩ ሳምንት ይፋ በሚደረጉ በተመረጡ ሜዳዎች ላይ ብቻ ይደረጋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትን የሚያገኘው ሊጉ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የሚከናወነው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ቀኑ በይፋ ባይገለፅም ምናልባትም ከሁለት ሳምንታት በኃላ በቀጥታ ስርጭት ዓለምአቀፉዊ ይዘት ባለው መልኩ ለማስተላለፍ መዘጋጀታቸውን አቶ ክፍሌ ሰይፈ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
“ፕሮግራሙን በጥሩ ሁኔታ ለማድረግ እያሰብን ነው፤ በቀጥታ ስርጭት ስለሚተላለፍ በጥሩ ሁኔታ ለማከናወን ጥረትም እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከነበሩት እጅግ የተሻለ የዕጣ አወጣጥ ፕሮግራም ይኖረናል፡፡ ዲ ኤስ ቲቪን አናግረን ዕጣ ማውጫውን ቀንም ወስነን ነበር። ሆኖም እነሱን እየጠበቅን ስለነበር ለጊዜው አራዝመነዋል፡፡ በዚህም አዲስ መርሐ-ግብር አወጣጥን ትመለከታላችሁ። ከዚህ ቀደም የነበረው አወጣጥ 16ቱ ክለቦች ይመጣሉ፤ አንደኛ ሁለተኛ እየተባለ ይወጣል፡፡ አሁን ግን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዕጣ ማውጣትን ነው የምናደርገው። ለዚህም የተሻለ ቦታ እያዘጋጀን ነው፤ በቅርቡ እናከናውነዋለን።” ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ገልፀውልናል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!