ከሳምንት በፊት አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረው ወልዲያ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር አከናውኗል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ላይ ተወዳዳሪ የሆነው እና ዳግም ወደ ነበረበት ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ወልዲያ ልምድ ያላቸውን አሰልጣኞች በደንብ አፈላልጎ ለመቅጠር በማሰብ የቅጥር ማስታወቂያን የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ አውጥቶ በርካታ አሰልጣኞችን ካወዳደረ በኃላ አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስን በዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ የቀድሞውን ኢትዮጵያ ውሀ ሥራ፣ ዳሽን ቢራ እና ጅማ አባ ጅፋርን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ ልምድ ያካበቱት አሰልጣኙ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማን በማሰልጠን የቆዩ ሲሆን አሁን ደግሞ ወልዲያን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅለዋል፡፡ ጠንካራ ቡድን ለመገንባት ጥረት እንደሚያደርጉም አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!