“አሁን ጥሩ መሻሻሎችን እያሳየሁ ነው” – ተስፈኛው አጥቂ የአብቃል ፈረጃ

የኢትዮጵያ የወጣቶች ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መንገድ መካሄድ ከጀመረበት ከ2008 ጀምሮ ለተከታታይ ዓመታት ዕድገቱን ጠብቆ በመጫወት የቆየው እና ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተ የሚገኘው ባለ ክህሎቱ ሁለገብ ተጫዋች የአብቃል ፈረጃ የዛሬው የተስፈኛ አምዳችን እንግዳ ነው።

ከመስመር አጥቂነት እስከ ፊት አጥቂነት ወደ ኃላም ተመልሶ የመስመር ተከላካይ በመሆን ጭምር የአዲስ አበባ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ከተመሰረተበት ከ2008 ጀምሮ በክለብ ደረጃ የታዳጊነት የእግርኳስ ዘመኑን አሳልፏል። ከ2010 ወዲህ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑን አፍርሶ ከ20 ዓመት በታች ቡድን በአዲስ መልክ ሲያቋቋም ይህ ተስፈኛ ወጣት ነበር። አዲስ አበባ ታዳጊ ቡድን ውስጥ በቆየባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ አብዛኛውን ጨዋታዎች ቡድኑን በአምበልነት መርቷል። በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ቡሩንዲ ላይ በተዘጋጀው የሴካፋ ዋንጫ የመጀመርያውን ጨዋታ አሸንፎ በኃላ በሦስት ተጫዋቾች ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ፈተና ባጋጠመው ቡድን ውስጥ አባል ነበር። ከ2012 ወዲህ ለኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን መጫወት የጀመረው የአብቃል በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። በተለይ ከወልዋሎ ጋር በነበረው ጨዋታ ዕይታውን ተጠቅሞ አቤል ከበደ ላስቆጠራት ጎል ያቀበለበት መንገድ አስገራሚ ነበር። ብዙ የመሰለፍ ዕድሎችን ያላገኘ ቢሆንም አልፎ አልፎ በተጫወተባቸው ጨዋታዎች አንድ ነገር ለማድረግ የሚጥር ተስፈኛ ወጣት እንደሆነ አሳይቷል። ፈጣሪ ፣ ፈጣን ፣ ታጋይ ፣ ጎል አስቆጣሪ ፣ ለቡድን አጋሮቹ ኳስን የሚያቀብል ፣ በየአንዳንዱ ጨዋታ የተለየ ነገር አሳይቶ ለመውጣት የሚጥር እንደሆነና ወደ ፊት ጠንክሮ ትኩረቱን እግርኳሱ ላይ አድርጎ ከሰራ ጥሩ ተጫዋች እንደሚወጣው ከወዲሁ መመስከር ይቻላል። በዛሬው የተስፈኛ አምዳችን ከዚህ ወጣት ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

“የተወለድኩት ኳስ-ሜዳ ነው። በተወለድኩበት አካባቢ ዓሊ ረዲ ፣ ብርሀኑ ቦጋለ (ፋዲጋ) ፣ አለምአንተ ካሳ ይገኛሉ። ኳስ ሜዳ ወደ ትምህርት ቤት በመቀየሩ እግርኳስ እየተጫወትኩ ያደግኩት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ነው። አበበ ቢቂላ ስታዲየም ለእኔ የእግርኳስ ዕድገት ትልቅ አስተዋፆኦ ያለው ሜዳ ነው።

“አሰልጣኝ ይገዙ እና መሐመድ በሚያሰሩት የታዳጊ ፕሮጀክት ውስጥ ስሰራ ቆይቼ ሙሉ ለሙሉ ቡድኑን አዲስ አበባ ከተማ ጠቅልሎ ሲወስደው እኔም ወደ አዲስ አበባ ገብቼ እጅግ ስኬታማ የሆነ በዋንጫ የታጀበ አምበል በመሆን ቡድኑን እየመራው ቆይታ አድርጌያለሁ። በኢትዮጵያ ቡናም ከ2012 ጀምሮ መጫወት የጀመርኩት። በኢትዮጵያ ቡና እስካሁን ባለኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ። በየጊዜው መሻሻሎችን እያሳየው ጥሩ ዕድገት ላይ ነኝ። አሰልጣኝ ካሳዬ በወጣት የሚያምን እና አሳማኝ እንቅስቃሴ እስካሳየው ድረስ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። አሁን ዝግጅታችንን በቀን አንድ ጊዜ እየሰራን ነው። ወደፊትም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እፈልጋለሁ።

“ከኢትዮጵያም ውጪ ወጥቶ መጫወት በጣም አስባለው። በእኔ እግርኳስ ህይወት ውስጥ ቤተሰቦቼ ያለ ምንም ጫና ሳያደርጉብኝ የምወደውን እግርኳስ ፍላጎቴ አድርጌ እንድጫወት በመፍቀድ እና በማበረታታት ስለረዱኝ አመሰግናቸዋለሁ። በተለይ አጎቴን እንዳለ ፍስሀን እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን ተነሳሽነት የፈጠረብኝ እርሱ በመሆኑ አመሰግነዋለው። በተወለድኩበት አካባቢ ያሉ የሠፈር ልጆች ፣ አሰልጣኝ ይገዙ እና መሐመድ እንዲሁም አብረውኝ ተጫወቱትን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!