ወልዋሎዎች ዝግጅት የሚጀምሩበት ቀን ታውቋል

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዝውውሩ ንቁ ተሳትፎ አድርገው ስድስት ተጫዋቾች ያስፈረሙት ወልዋሎዎች ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ አድርገዋል።

ክለቡ ተጫዋቾቹ እንዲሰበሰቡ ጥሪ ያደረገ ሲሆን የኮቪድ 19 ምርመራ ከተደረገላው በኋላ ጥቅምት 17 ዝግጅት እንደሚጀምሩ ታውቋል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በወልዋሎ ስታዲየም እድሳት ምክንያት በመቐለ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ያካሄዱት ቢጫዎቹ ዘንድሮ ግን በከተማቸው ዓዲግራት ዝግጅት የሚጀምሩ ይሆናል።

እስካሁን ድረስ ዓወት ገብረሚካኤል፣ ወንድወሰን አሸናፊ፣ አስናቀ ሞገስ፣ ዳንኤል ደምሱ፣ ሽመልስ ተገኝ እና አብዱልበሲጥ ከማልን ያስፈረሙት ቢጫ ለባሾቹ ከቀናት በኃላ የነባር ተጫዋቾች ውል ማራዘም ይጀምራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ የቴክኒካል ዳይሬክተር እና ቡድን መሪ ቅጥር አውጥቶ እስካሁን ድረስ ሒደቱን ያላጠናቀቀ ሲሆን በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ያጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ