የዕድሜ ቡድኖች የሚሳተፉበት የሴካፋ ውድድር የምድብ ድልድል ወጥቷል

የኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች በሴካፋ ውድድር በሞት ምድብ መደልደላቸው ታውቋል።
2007 ላይ ተጀምሮ ለአራት ጊዜያት የተደረገው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ዘንድሮም እንደሚከናወን ታውቋል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሀገራትን ታሳቢ በማድረግም የውድድሩ አዘጋጅ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብር አከናውኗል። በዚህም በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ 2 ከዩጋንዳ እና ኬንያ ጋር ተደልድሏል። በተመሳሳይ ሩዋንዳ፣ ኤርትሪያ እና ደቡብ ሱዳን በምድብ 1 እንዲሁም ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ታንዛኒያ በምድብ 3 መደልደላቸውን የውድድሩ አዘጋጅ አስታውቋል። የየምድቦቹ የበላይ የሆኑ ቡድኖች እና ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ የሚመረጠው ቡድን ወደ ግማሽ ፍፃሜ ግጥሚያ እንደሚያልፉም ተጠቁሟል።

በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ከታህሳስ 13 – 28 በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ የሚሆነው እና ሁለተኛ የሚወጣው ቡድን የምስራቅ እና መካከለኛውን ቀጠና ወክሎ በ2021 በሞሮኮ በሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ በቀጥታ እንደሚሳተፍ ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና ሴካፋ ከህዳር 22 – ታህሳስ 6 በታንዛኒያ አስተናጋጅነት የሚደረገውን ከ20 ዓመት በታች ውድድርንም የምድብ ድልድል አውጥቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከኬንያ እና ሱዳን ጋር በምድብ 3 ሲደለደል ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱማሊያ እና ጂቡቲ በምድብ 1 እንዲሁም ቡሩንዲ፣ ኤርቲሪያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ በምድብ 2 ተደልድለዋል።

በታንዛኒያ በሚደረገው ውድድር ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ የትኛውም ቡድን እስካሁን ማረጋገጫ እንዳልሰጠ ሲገለፅ በውድድሩ ተሳትፎ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን ግን በ2021 በሞሪታኒያ አስተናጋጅነት በሚደረገው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ በቀጥታ እንደሚሳተፍ ተነግሯል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ግን በትላንትናው ዕለት ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን እንዲመራ አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን መምረጡን መገለፁ ይታወሳል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ