የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ዴቪድ በሻህ በአሁኑ ወቅት የእግር ኳስ አማካሪ እና ወኪል ሆኖ እየሰራ ይገኛል። በZoom ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለሥራው እና በተለይም ስለ ትውልደ ኢትዮጵያን ተጫዋቾች ተወያይቷል።
በኮልኝ ከተማ ስለነበረው ዕድገትህ ትንሽ ንገረን!
እንዳልከው የተወለድኩት እና ያደኩት በኮሎኝ ከተማ ነው። ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት በጀርመን አራተኛ ዲቪዚዮን ተጫውቼ ነበር።
የ2013 ብሐራዊ ቡድን አባል ነበርክ …
አዎ። ምንም እንኳን ወደ መጨረሻው ውድድር ባልሳተፍም ለማለፍ በሚደረገው ዝግጅት ላይ ተጠርቼ ነበር። በዛን ወቅት የነበረው የደጋፊ ስሜት እጅግ በጣም ደስ የሚል ነበር ። አሰልጣኞቹም በወቅቱ አባቴን ሲያናግሩት እና ለኢትዮጵያ እንድጫወት ሲጠሩኝ ብዙም አልጓጓሁም ነበር። ነገር ግን ሃሳቤን ልቀይር ችያለሁ።
በኢትዮጵያ እና በስኬታማው ጀርመን መካከል ያለው የአሰለጣጠን ልዩነት ምን ይመስላል?
ስለኢትዮጵያ የታዳጊዎች አሰለጣጠን ለማውራት ይከብደኛል። ምክንያቱም በዛ ሲስተም ስላልተጫወትኩ። በአጠቃላይ ግን ልዩነቱ ታክቲካዊ ነው። እዚህ ስመጣም የከበደኝ ነገር እዚህ ካሉ ተጫዋቾች የጨዋታ ስልት ጋር መላመድ ነበር። አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ባላምንባቸውም ከቡድን አጋሮቼ ጋር ለመላመድ ስል ማድረግ ነበረብኝ። ከባድ ነበር፤ ግን እንደማንኛውም የህይወት አካል ትላመዳለህ። ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች አይለፉም በማለት ይተቿቸዋል። ነገር ግን በጣም ታታሪዎች ናቸው። በዚህ አይታሙም። ጀርመን እያለሁ በማለዳ 12 ሰዓት ልምምድ ሰርቼ አላውቅም። ነገር ግን እዚህ ያጋጠመኝ ያ ነበር።
በአንድ ወቅት የጉልበት ጉዳት አጋጥሞህ ነበር..
ኢትዮጵያ ከመምጣቴ 3 ዓመታት በፊት የጅማት ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። በወቅቱ ቀዶ ጥገናም አድርጌ ነበር። ነገር ግን ካገረሸ ከጨዋታ እንደሚያርቀኝ አስቤ ነበር። ደግነቱ የተጫዋችነት ጊዜዬን ስጨርስ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቅ ስለነበር እና በስፖርት ማኔጅመንትም የያዝኩት ዲፕሎማ ስለነበር ሽግግሩ ከባድ አልነበረም።
ስለ አሁኑ ሥራህ ንገረን ?
በመጀመሪያ ቡና ለመሥራት ነበር ያሰብኩት። ግን አልተሳካም። በመሆኑም የእግር ኳስ አማካሪ ድርጅት አቋቁሜያለሁ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቁ ችግር አስተዳደር ነው። አዲስ በሚያድጉት እና በነባር ክለቦች መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ አይደለም። ሌላው የሚስተዋለው ችግር ደግሞ ክለቦቹ ቋሚ የሆነ ገቢ ከመንግሥት አልያም ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ስለሚያገኙ በርትተው ለመሥራት እና ተጨማሪ ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ተነሳሽነት የላቸውም። ብር እንደሚመጣ ካወቅህ ለምን ትለፋለህ?
ፌደሬሽን የሚሰሩ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ። ነገር ግን ሥራው ላይ እከል ገጥሞኛል። ለምሳሌ የገንዘብ ጉዳይ እንደችግር ይቀርባል። ግን ሥራውን ከሰራን በኋላ ገንዘብ የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ እየተቻለ ይህን እንደምክንያት ማቅረብ አግባብ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የኔ የሥራ ሀሳብ ሲሳካ ገንዘቡም አብሮ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ።
ለፌደሬሽኑ ይፋዊ የሆነ ፕሮፖዛል አስገብቼ ነበር። ፌደሬሽን የሚሰሩ ሰዎችንም በአካል ተገኝቼ አናግሬያቸው ነበር። ሆኖም ግን ይሄ ነው ችግሩ ወይ ደግሞ መሰናክሉ ብለህ የምትነጥለው ጉዳይ የለም።
ስለ ትውልደ ኢትዮጵያን ተጫዋቾች ምን ትላለህ ?
ትውልደ ኢትዮጵያን ወደ ብሔራዊ ቡድን የሚመጡበት መንገድ ትክክለኛ ነው ለማለት ያስቸግራል። እኔም የተጠራሁበት መንገድ መሠራት ባለበት ሁኔታ አልነበረም። የዛኔም አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ናቸው። በመልማዮች አልታየሁም ነበር። አኸን የታዳጊ ቡድን ውስጥ ነበር የምጫወተው እና እዛ የነበረ ሰውነትን የሚያውቅ ሰው ነው አናግሮኝ ሁኔታዎችን ያመቻቸው። በዛን ወቅት በፓስፖርት ችግር ምክንያት መጫወት አልቻልኩም እና ይህ ችግር አሁንም አለ። ሁለተኛ ጊዜም ስጠራ በአግባቡ ሳይሆን በዘፈቀደ ነበር። ዝም ብለው ና ተጫወት ነው ያሉኝ። ወደ ብሄራዊ ቡድን ከመቀላቀልህ በፊት የሙከራ ጊዜ ውስጥ ማለፍ ሲኖርብህ ግን አልተደረገም። እንዲሁ የማውቀው አሪፍ ተጫዋች አለ የጓደኛዬ የህቱ ልጅ ነው እና የመሳሰሉት ነገሮች እየተባሉ ነው የሚጠሩት ተጫዋቾች። ከዛ የመጣው ተጫዋች በደንብ ሳይጫወት ሲቀር አይ አይችሉም ውጪ ያሉት ይባላል። ሲስተሙ እንደዚህ አይደለም መሆን ያለበት።
በአሁኑ ወቅት ወደ 7ዐ የሚጠጉ ተጫዋቾች አግኝቻለሁ። በቀጥታ ያላናገርኳቸው ብዙ አሉ ነገር ግን መረጃቸውን ሳሰባስብ ነበር። ሁሉም ለኢትዮጵያ መጫወት ላይፈልጉ ቢችሉም በዛው ልክ መጫወት የሚፈልጉ ብዙ አሉ። አሁን በጀርመን ስለምገኝ ያለውን ክፍተት መድፈን እና የመገናኛ መስመር መሆን እችላለሁ። ከአሁኑ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ተስፋ ሰጪ ውይይት አድርገናል።
ከዴቪድ በሻህ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቆይታ ሊንኩን በመጫን YouTube ላይ መመልከት ትችላላችሁ።
https://youtu.be/4fGjioD350o
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!