“ሳልፈልግ ነው ለጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን የተጫወትኩት” አብዲ መሐመድ

በቅርቡ በከፍተኛ ሊግ ለሚሳተፈው መከላከያ ፊርማውን ያኖረውና ለጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው አብዲ መሐመድ ስለ እግርኳስ ህይወቱ፣ ለጅቡቲ ስለመጫወቱ እና ቀጣይ አላማው ይናገራል።

ድሬደዋ ከተማ ልዩ ስሙ ኮኔል አሸዋ አካባቢ ተወልዶ የእግርኳስ ህይወቱን በ2007 በድሬደዋ ከተማ ተስፋ ቡድን መጫወት ጀምሯል። ድሬዳዋ ዳግመኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት በ2008 ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ አሰልጣኝ መሠረት ማኒ እስከነበረችበት ጊዜ ድረስ በመጠኑም ቢሆን የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ ተጫውቷል። ድሬዳዋ የአሰልጣኝ ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ የመሰለፍ እድል በማጣት ወደ እናቱ ሀገር ጅቡቲ በመሄድ አርት ሶላር 7 (Arta solar7) ለተሰኘ ክለብ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ተጫውቷል። በቆይታውም የሀገሪቱ ሊግ ዋንጫን ከማንሳቱ በተጨማሪ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ ለመጫወት ችሏል። በዚህ ያላበቃው አብዲ የጅቡቲ ቆይታ ለብሔራዊ ቡድን በመመረጥ በ2019 የቻን ውድድር ማጣርያ በኢትዮጵያ በድምር ውጤት 5-4 በተረታው ቡድን ውስጥ ጅቡቲን በመወከል ከትውልደባት ሀገር ተቃራኒ ሆኖ ተጫውቷል። አሁን ወደሚወዳት ሀገሩ በመምጣት በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ለሆነው መከላከያ ፊርማውን በማኖር በቢሸፍቱ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ስለጅቡቲ ቆይታው እና የወደፊት እቅዱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።


ትውልድ እና እድገት

የተወለድኩት ድሬዳዋ ነው። በአባቴ ኢትዮጵያዊ፤ በእናቴ ጅቡቲ ነኝ። ድሬዳዋ ኮኔል አካባቢ በሚገኝ ሜዳ ስጫወት ቆይቼ ተስፋ ቡድን በ2007 ከተጫወትኩ በኋላ በዓመቱ ወደ ላይ አድጌ አሰልጣኝ መሠረት ማኒ በፕሪምየር ሊጉ በተወሰኑ ጨዋታዎች የመሠለፍ እድል አግኝቼ እጫወት ነበር።

ወደ ጅቡቲ የሄደበት ምክንያት

ሁለት ምክንያት ነው። የመጀመርያው ድሬዳዋ አንዳንድ ከፀጥታ ጋር ተያይዞ አለመረጋጋት ስለነበር እናቴ ጋር ለመቆየት ጅቡቲ ሄድኩ። ዋናው ግን ድሬዳዋ የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረጉ የመጫወት እድል እያጣሁ ስመጣ በዚህም ተስፋ ቆርጬ ነው ወደ ጅቡቲ የሄድኩት።

የጅቡቲ ቆይታ

ጅቡቲ እያለው ስለኔ መረጃ ነበራቸውና አርታ ሶላር 7 ክለብ ሰዎች እንድጫወትላቸው ጠየቁኝ። እሺ ብዬ መጫወት ጀመርኩ። ከክለቡ ጋር የሀገሪቱ ሻምፒዮን ሆንኩ። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ በታሪክ አጋጣሚ ለመጀመርያ ጊዜ ከሱዳን ቡድን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ መጫወት ቻልኩ። ይህ ለኔ በጣም ትልቅ እድል ነበር።

ለጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ

በክለብ ስጫወት የተመለከተኝ የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጥሪ አቅርቦልኝ ለመጫወት ችያለው። እኔ ለጅቡቲ ብዙም የመጫወት ፍላጎት አልነበረኝም። ምክንያቱም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ሆኖም በተደጋጋሚ ግፊት ሲያደርጉብኝ ለመጫወት ተገድጃለሁ። በአጋጣሚ የቻን ማጣርያ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመደልደል ቻልን። የመጀመርያውን ጨዋታ ጅቡቲ ላይ ተቀይሬ በመግባት መጫወት ችያለው። የመልሱን ጨዋታ ድሬ ላይ ከቡድኑ ጋር አብሬ ብመጣም ጉዳት አጋጥሞኝ ሳልጫወት ቀርቻለው።

ከኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጋር የተፈጠረው ገጠመኝ

ጅቡቲ ላይ በነበረው ጨዋታ ተቀይሬ ወደ ሜዳ ገብቼ ስጫወት ስማቸውን የማላቀው ባያቸው ግን የምለያቸው ሁለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አማርኛ ቋንቋ የማላውቅ መስሏቸው አሁን ለሚዲያ እንዲህ ነው የማትለው ነገር የእኛ ተጫዋቾች ጋር ሲነጋገሩ “እናንተ ምንድነው እንዲህ የምትሉት?” ስላቸው ደንግጠው “አንተ አማርኛ ትችላለህ እንዴ?” ብለው ተያይተው የሳቁበት አጋጣሚ ሁሌም ይገርመኛል።

የጅቡቲ ሊግ የክለቦች ደረጃ

እንደ ኢትዮጵያ አይደለም። ማንም እግርኳስን እንደመደበኛ ፕሮፌሽን አይመለከተውም። ሁለተኛ ሥራቸው ነው። በአብዛኛው ወታደር፣ መምህር፣ ነጋዴ በሌላም ሙያ የተሰማራ በእረፍት ጊዜው የሚጫወት ነው። ሊጓም በጣም ደካማ እና አስር ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

የመከላከያ ቆይታ

በቢሸፍቱ ጥሩ የዝግጅት ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። የክለቡ ዋና እቅድ ወደ ፕሪምየር ሊግ መመለስ ስለሆነ ይህን ለማድረግ ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው።

ቀጣይ እቅድ

ከሦስት ዓመት በኋላ ወደ ሀገሬ መጥቼ የመጫወት እድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ያለኝን አቅም ተጠቅሜ መከላከያን በማገልገል ለብሔራዊ ቡድን ሀገሬን ወክዬ መጫወትን አስባለው። ይህን ለማድረግ የሚከለክለኝ የካፍም የፊፋም ህግ የለም፤ የሁለት ሀገር ዜግነት ያለኝ በመሆኑ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ