መቐለ 70 እንደርታ ተከላካይ አስፈረመ

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የሆኑት መቐለ 70 እንደርታዎች ግዙፉን ማሊያዊ ተከላካይ አስፈርመዋል።

በዚህ ክረምት ከበርካታ ተከላካዮች ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ የኋላ ክፍላቸውን በአዲስ መልኩ እንደሚያዋቅሩ የሚጠበቁት መቐለዎች በቦታው ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት ማሊያዊው ተከላካይ አዳማ ሲሶኮን ምርጫቸው አድርገዋል። በ2010 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በመጀመርያ ዓመት ቆይታው ከጅማ አባጅፋር ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ይህ ተከላካይ ባለፈው ዓመት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ካሳለፈ በኋላ ከቀድሞ አሰልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ዳግም ለመሥራት ወደ መቐለ አምርቷል።

በ2011 ከጅማ አባጅፋር ጋር በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የነበረው ሲሶኮ ዘንድሮም ዳግም በውድድሩ የመሳተፍ ዕድል ከማግኘቱ በተጨማሪ ቡድኑ ባለፈው ዓመት የነበረው የአየር ኳስ ችግር ለመቅረፍ ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!