“በገድ ወይም በአጉል እምነት የማምን ሰው አይደለሁም” አሰልጣኝ ሕይወት አረፋይነ
በእግርኳስ ዙርያ የሚሰሙ አጉል እምነቶች ወይም እንደ ጥሩ ዕድል ምልክት ተቆጥረው የሚደረጉ ተግባራት በርካታ ናቸው። ምንም እንኳ በሃገራችን እግርኳስ በይፋ የሚሰሙ መሰል ተግባራት እምብዛም ባይሆኑም ተመሳሳይ ነገሮች እንደማይጠፉ ለመገመት አይከብድም። በዓለም አቀፍ እግርኳስ የሚሰሙ ተመሳሳይ ተግባራትም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከነዚህ ውስጥ አይቮሪኮስታዊው የቀድሞ የአርሰናል ተከላካይ ኮሎ ቱሬ ወደ ሜዳ ሲገባ “መጨረሻ ካልገባሁ ጥሩ ዕድል አይገጥመኝም” ብሎ ያምናል። ሌላው የቀድሞ የቼልሲ ተከላካይ ጆን ቴሪም ሁልጊዜ ከጨዋታ በፊት የአሸርን ሙዚቃ መስማት እንደ የጥሩ ዕድል ምልክት አድርጎ እንደሚወስደው በአንድ ወቅት ገልፆ ነበር።
ለዛሬ በዚህ ዙርያ ልናነሳው የወደድነው ደግሞ የመቐለ 70 እንደርታ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሕይወት አረፋይነ ዘወትር ከጨዋታ በፊት የምታደርገው አነጋጋሪ ተግባር ነው። በትግራይ ስታዲየም የሚታደሙ እና ለሴቶች እግርኳስ ቅርብ የሆኑ የእግርኳስ ቤተሰቦች የሚያነሱት ተደጋጋሚ ጥያቄ አለ። “አሰልጣኝ ሕይወት ከጨዋታ በፊት የተጫዋቾቹን ግንባር ለምንድነው የምትመታው ? ነገሩ አጉል እምነት ነው ወይስ …?” የሚል። በጉዳዩ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረገችው አሰልጣኟ ሃሳብዋን በዚህ መልኩ ገልፃለች።
“ተግባሩን ከድሮ ጀምሮ ነው የማደርገው። ግን ከአጉል እምነት ወይም ከገድ ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም። አላማው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ግን የተጫዋቾቼ ተነሳሽነት ለመጨመር ወይም ለሞራል ነው። ግንባራቸው መምታት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳቸው በጨዋታ ላይ ያላቸውን ክፍተት ወይም ደካማ ጎን እየነገርኩ ነው ግንባራቸውን መትቼ ወደ ጨዋታ የማስገባቸው። ብዙ ሰዎች በሁኔታው ሊገረሙ ወይም ከአጉል እምነት ጋር ሊያያይዙት ይችላሉ። ግን በፍፁም ከእምነት ጋር የተያያዘ ነገር የለውም። በገድ ወይም በአጉል እምነት የማምን ሰውም አይደለሁም፤ ሜዳ ላይ የሚፈጠረው ሁሉም ነገር የሥራ ውጤት እንጂ በአጉል እምነት የሚቀየር ነገር የለም።”
በእግርኳስ ተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ላለፉት ሃያ ዓመታት የቆየችው እና በቅርቡ በእግርኳስ ስልጠና የማስተርስ ዲግሪዋን ያገኘችው ኢንስትራክተር ሕይወት አረፍይነን በሴቶች ገፅ ዓምዳችን በመጪው ሀሙስ ይዘን እንቀባለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!