ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤሌክትሪክ አራት ተጫዋቾች አስፈረመ

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆኑት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የአራት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀዋል።

ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ከአዳማ ከተማ ጋር ቆይታ በማድረግ ክለቡ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች የሆነችው እፀገነት ማረፍያዋ በሊጉ የተሻሉ ተፎካካሪ ለመሆን በጥረት ላይ ላሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሆኗል። ከዚ በፊት በደደቢት፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ የተጫወተችው አማካይዋ ከሦስት የተለያዩ ክለቦች የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አንስታለች።

ሣራ ነብሶ ከአዳማ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተቀላቀለች ሌላኛው ተጫዋች ነች። የቀድሞዋ የጌዴኦ ዲላ አጥቂ በአዳማ ለመቆየት ተስማምታ የነበረ ቢሆንም በይፋ የኤሌክትሪክ ተጫዋች ሆናለች። ለቡድኑ የማጥቃት ክፍል ጥሩ ግብአት ትሆናለች ተብሎም ይጠበቃል።

ሲሳይ ገብረዋህድ ሌላዋ ፈራሚ ናት። የአካዳሚ ውጤት የሆነችው ባለ ክህሎቷ አማካይ ቀደም ብላ አዳማ ከተማን ለመቀላቀል ተስማምታ የነበረች ቢሆንም ወደ ኤሌክትሪክ ማምራቷ ተረጋግጧል።

ልደት ቶሎአ የማጥቃት ተጫዋቾችን በማዘዋወር ላይ ትኩረቱን ያደረገው ኤሌክትሪክን የተቀላቀለች ሌላዋ አዲስ ፈራሚ ናት። የአጥቂ ሥፍራ ተጫዋቿ ከዚህ ቀደም ለተዋሳ ከተማ መጫወት ችላለች።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!