በሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገዱት ዋልያዎቹ ዳግመኛ ሌላ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው።
በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ 2022 ለተሸጋገረው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በቀጣዮ ወር መጀመርያ ቀናት ከኒጀር ጋር የሚጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ከዛምቢያ ጋር ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ስታዲየም በማከናወኑ ሽንፈት ማስተናገዳቸው ይታወቃል። ከመጀመርያው ጥሪ አስር ተጫዋቾችን የቀነሱት አሰልጣኝ ውበቱ ተጨማሪ አንድ የአቋም መለኪያ ጨዋታ በማድረግ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ለመለየት እንዲረዳቸው ካሜሩሮ ወይም ከደቡብ ሱዳን ጋር ለጨዋታ ጥረት ላይ መሆናቸውን ሰምተናል።
የሁለቱም ሀገራት ፌዴሬሽኖች አስፈላጊውን ነገር ኢትዮጵያ ማሟላት ከቻለች ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን በኢሜይል ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ አሳውቀዋል። ጉዳዩን እያጤነ የሚገኘው ፌዴሬሽኑም ከሁለቱ ሀገራት መካከል አንዱ ጋር ለመጫወት በቅርቡ አንድ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!