የግል አስተያየት | የአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ግላዊ መስተጋብር

በሃገራችን እግርኳስ የአሰልጣኞች እና የተጫዋቾችን ግላዊ ግንኙነት በተመለከተ በአንዳንዶች ዘንድ የሚሰነዘር የተለመደ አባባል አለ፡፡ “ተጫዋቾችን አትቅረብ፤ ይንቁሃል!” የሚል፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህንን “ምክር” ደጋግመው ሲናገሩት ይደመጣል፡፡ እርግጥ ነው ቅርበቱ ገደቡን ያለፈ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ያልጠበቀ፣ ስፖርታዊ ኃላፊነትን ያላማከለ፣… ከሆነ ማስናቁ አይቀሬ ነው፡፡ በአሰልጣኞችና በተጫዋቾች መካከል አግባብነት ያለው፣ የመከባበር ወሰኑን ያላለፈና ውጤት ተኮር የሆነ ግንኙነት መገንባቱ የተጫዋቾቹን ሁለንተናዊ እድገት ያረጋግጣል እንጂ ጉዳት አያስከትልም፡፡ በእኔ እምነት አሰልጣኞችን በተጫዋቾች እንዲናቁ የሚያደርገው ብቸኛው ነገር የመጥፎ ስብዕና ባለቤት ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ከተጫዋቾች ጋር አብሮ አልኮል ነክ መጠጦችን የሚጎነጭ፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትንም ይሁን ተጫዋችን የሚያማ፣ አላግባብ ተጫዋቾችን የሚሳደብ፣ የሚዋሽ፣ የሚያስመስል፣ ከንቱ ውዳሴ የሚያበዛ፣ በራሱ የማይተማመን እንዲሁም የልምምድ ሰዓት የማያከብር እና ተዘጋጅቶ የማይመጣ አሰልጣኝ በተጫዋቾቹ ዘንድ ከበሬታ ሊያገኝ አይችልም፡፡

ማንኛውም አሰልጣኝ ከተጫዋቾቹ ጋር ጥሩ ተግባቦት ይፈጥር ዘንድ ለሁሉም ተጫዋቾቹ ቀና አመለካከት ሊኖረው ይገባል፡፡ ለጥረታቸው ዋጋ መስጠት፣ ለስብዕናቸውም ክብር ሊያሳይ የግድ ይላል፡፡ ሁኔታዎች በመልካም መንገድ ሲሄዱ ተጫዋቾች አድናቆት ወይም ሙገሳ ይፈልጋሉ፤  ስህተት ሲፈጽሙም ተግሳጽ ሊሰሙ የተዘጋጁ እንዲሆኑ የአሰልጣኙ ድርሻ የላቀ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ተጫዋቾች ከአሰልጣኞቻቸው የሚፈልጉት ፍትሃዊ፣ ቆራጥ፣ አዋቂ፣ ሆደ ሰፊ እና ጥሩ መሪ እንዲሆኗቸው ነው፡፡ ውስጣቸው ያለውን ህልም እውን ያደርጉ ዘንድ እንዲያግዟቸውም አጥብቀው ይመኛሉ፡፡

አሰልጣኞች ከግላዊ ፍላጎታቸው በላቀ ለቡድን ግንባታና ለተጫዋቾቹ የእግርኳስ ህይወት ዕድገት ሲታትሩ ማየት እጅጉን የሚያስመሰግናቸው ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይህን በማድረጋቸው በተጫዋቾቻቸው ልዩ ክብር ያሰጣቸዋል፡፡ ተጫዋቾች ለሚተልሙት ሩቅ ግብ የማድረስ አጋዦቹ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ አሰልጣኞች የሙያ ብቻ ሳይሆን የህይወት መንገድ ቀያሾችም ናቸው፡፡  እነርሱ ኮትኩተው የሚያሳድጓቸው ታዳጊዎች ከተሳካላቸው በዓለምአቀፋዊው የእግርኳሱ መድረክ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን እና ሃገራቸውን  የሚያስጠሩ ዜጎች ይሆናሉ፡፡ በተጫዋችነት በለስ የሚቀናቸው ጥቂቶች በመሆናቸው የቀሩት በሌላ  የኑሮ መንገድ ቢጓዙ የተሳካ ህይወት እንዲኖራቸው የአሰልጣኞቻቸው ድርሻ ጉልህ ነው፡፡ አሰልጣኝነት በሰልጣኞች አዕምሮ ውስጥ የማሸነፍ እና የመሸነፍን ልዩነትን የማስተማር ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ ተጫዋቾችን የጤናማ አካል፣ ጤናማ አዕምሮ፣ ጤናማ ሥነ ልቦና ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ለፈተና የተዘጋጁ፣ ተስፈኞች ፣ ንቁዎችና ለመልካም ሃገራዊ እሴቶች በጎ አተያይ ያላቸው ብቁ ዜጎች ማፍራትም የአሰልጣኝነት ሙያ ተዘዋዋሪ ሚና ይሆናል፡፡

በተለይ ታዳጊዎችን ስናሰለጥን የነገዎቹን እግርኳስ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን በተለያየ ዘርፍ የሚሰማሩ ባላሞያዎችን፣ የቤተሰብ፣ የግዙፍ ተቋማት፣ የትልልቅ ድርጅቶችና የሃገር መሪዎች ጭምር እንደምናሰለጥን አውቀን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ እዚህም ላይ በአሰልጣኝና በተጫዋች መካከል የሚኖር አዎንታዊ ግንኙነት ለታዳጊ ተጫዋቹ እግርኳሳዊ እድገት እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ እግርኳስን የሚያዘወትሩ ታዳጊዎች አብዛኞቹ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ታዳጊ ተጫዋቾች ወደ ልምምድ ሜዳ ሲመጡ በብዙ ነገር ተፈትነው ነው፡፡ ህይወት ለእነርሱ አልጋ በአልጋ አይደለችም፡፡ ከቤተሰብ በሚነሳ ተቃውሞ፣ በምግብ እና በትርንስፓርት እጦት፣ በመጫወቻ ጫማ እና ሌሎች መገልገያ መሳሪያዎች እጥረት በብርቱ ይቸገራሉ፡፡ በኑሮአቸው ሻል ያሉትም ቢሆኑ በመሰረታዊ ነገሮች ባይቸገሩም ከብቃት መውረድና ከእድሜ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ፃታዊ ግንኙነቶችና ሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች ይጨነቃሉ፡፡

እነዚህንና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን የሰልጣኞች ተግዳሮቶች ማስተዋል ከቻልን በርካታ ተጫዋቾች ለልምምድም ይሁን ለጨዋታ ወደ ሜዳ ሲመጡ በበርካታ አሉታዊ ተፅእኖዎች ስር እንደሚያልፉ ማሰብ እንችላለን፡፡ ተጫዋቾቻችን የተሸከሟቸው ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመስራት ፍላጎታቸውን በመገደብ፣ ተነሳሽነታቸውን እንዲያጡ በማድረግ እና በራስ መተማመናቸውን በማውረድ ለውጤታማነት እንዳይተጉ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል፡፡ በሃገራችን እግርኳስ ይህን ችግር ሊጠቁምና መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል ጥናት ስለመደረጉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ጉዳዩ ግን የተናጠልም ሆነ የቡድንን ውጤታማነት ስለሚገድብ እንዲሁ በቀላሉ መታየት የሌለበት እና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥው የሚገባ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በአሰልጣኞችና በተጫዋቾች መካከል አክብሮታዊ ግንኙነት መመስረት የሚኖረውን ጥቅም በጥቂቱ ለመጠቆም ከፍተኛ ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ የተጫዋቾች ችግር ተካፋይ ስንሆን ከዛሬያቸው ይልቅ ነገአቸውን የማየት ዕድል እንሰጣቸዋለን፡፡ ሥነ ልቦናዊ ድክመታቸውንም እንቀርፍላቸዋለን፡፡ 

በሃገራችን አብዛኞቹ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ  ተጫዋቾች ከአቋም መውረድ፣ ልምምድ ለመስራት ፍላጎት ከማጣት፣ ከጉዳት እና ከሚገጥማቸው ሌሎች ግላዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ ከአሰልጣኞቻቸው ጋር ተኳርፈው ረጅም ጊዜ ያባክናሉ፡፡ በችግሮቻቸው ዙሪያ ተወያይተው መፍትሄ ማግኘት ሲችሉ እንዲሁ ባለመነጋገር  አብሮ ለመዝለቅ ይወስናሉ፡፡ ይህ ለእኔ በጣም አስገራሚ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ነው፡፡ አሰልጣኞች ከተጫዋቾቻቸው ከፍተኛውን ብቃት ለማግኘት ሲሉ እንዴት ጥሩ ግንኙነት አይመሰርቱም?

በእርግጥ ከላይ እንዳነሳሁት ከተጫዋቾች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በጣም ጥንቃቄ የሚሻና አመራር ላይ ችግር እንዳይፈጥር ሚዛኑን የጠበቀ መሆን ይገባዋል፡፡ ተጫዋቾቹ ያሉብትን የብቃት ደረጃ ማሳወቅና ማበረታታት፣ ሙያዊ ግንኙነት መፍጠር፣ እውነተኛ ፍላጎትን ማሳወቅ፣ በችግር ጊዜ ከጎናቸው ለመቆም መዘጋጀት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች የተጫዋቾች እግርኳሳዊ ብቃት ለማሳደግ አልፎም ሁለንተናዊ እድገታቸውን ስኬታማ እንዲሆን ለማስቻል ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በእግርኳስ ባደጉት ሃገራት በተደረጉ በርከት ያሉ ጥናቶች አሰልጣኞች ከተጫዋቾች ጋር የሚኖራቸው አዎንታዊ ግንኙነት የተጫዋቾችን የግል እንዲሁም የቡድንን ብቃት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድጉ ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚስተዋለው  የአሰልጣኞችና የተጫዋቾች አመርቂ ያልሆነ ሙያዊ ግንኙነት ሊሻሻል ይገባል፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ተጫዋቾችን ብቻ ሳይሆን የነገዎቹን ሃገር ተረካቢዎች እንደምናሰለጥን አውቀን እነርሱን የምናዳምጥበት ጊዜ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ጥሩ እይታ ኖሯቸው በልምምድም ይሁን በጨዋታ ላይ እኛ ያላስተዋልንውን ነገር የሚያዩ ግን ደግሞ ሊያናግሩን ፍርሃት የሚሰማቸው አንዳንድ ተጫዋቾች አሉ፡፡ እነዚህንም እናቅርባቸው፤ በአሰልጣኞች እና በተጫዋች መካከል ያለውን ግድግዳ እናፍርስ፤ የመግባባት ድልድዩን እንገንባ!!!

© ሶከር ኢትዮጵያ


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡