ሪፖርት | ዋልያው በሜዳው ሚዳቆዋ ላይ ድል ተቀዳጅቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኒጀር አቻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናግዶ በድንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል አግኝቷል።

ዳውዱ ዊልያምስ የመሩትን ይህንን ጨዋታን ለመከታተል የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የኒጀር እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ሃሚዱ ጅብሪል እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከአራት ቀናት በፊት ወደ ኒያሜ አቅንተው አንድ ለምንም የተረቱበትን ቋሚ 11 ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ተክለማርያም ሻንቆ፣ ሱሌማን ሀሚድ፣ አስቻለው ተመነ፣ ያሬድ ባዬ፣ ረመዳን የሱፍ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አቡበከር ናስር፣ ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በ4-3-3 የተጫዋች አደራደር በማሰለፍ ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው በጀመረ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያለመረጋጋት እና ኳስን ቶሎ ቶሎ የመነጣጠቅ እንቅስቃሴ ሲታይ ነበር። ነገርግን በ7ኛው ደቂቃ በጨዋታው ለግብነት የቀረበ ሙከራ በአቡበከር ናስር አማካኝነት ያደረጉት ዋልያዎቹ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መግባት ጀምረዋል። በተለይ አቡበከር ለግብ ጠባቂው ትይዩ የነበረውን ኳስ ከሞከረ በኋላ ኳስን በመቆጣጠር አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በላይኛው የሜዳ ክልል (የኒጀሮች) ማሳለፍ ይዘዋል። በ14ኛው ደቂቃም ሽመልስ በቀለ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በጥሩ ቅንጅት እየተቀባበሉ ወደ ሳጥን ገብተው የተገኘውን አጋጣሚ አማኑኤል ወደ ጎልነት ቀይሮ መሪ ሆነዋል። ይህንን ጎል አማኑኤል ካስቆጠረ በኋላም ሜዳ ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ያሳዩት የደስታ አገላለፅ አስደናቂ ነበር።

የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ የቀጠሉት ዋልያዎቹ መሪ የሆኑበትን ግብ ካስቆጠሩ ከደቂቃ በኋላም ሌላ ጎል ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በዚህም ሽመልስ ከቀኝ መስመር ሱሌማን ያሻገረለትን ኳስ ተቆጠቀጥሮ ወደ ግብ ሊመታው ሲል ግብ ጠባቂው ፈጥኖ በመውጣት ዕድሉን አምክኖበታል። በተጨማሪ በ20ኛው ደቂቃም አቡበከር ጥሩ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ቡበከር ሀይንኮዬን ብቻ ፊት በመተው በራሳቸው ክልል በመሆን ክፍተቶችን ለመዘርጋት ሲታትሩ የነበሩት ኒጀሮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ብዙም ፍላጎት ሳያሳዩ ጨዋታውን ቀጥለዋል። ይልቁንም ኳሱን ለተጋጣሚያቸው በመተው የዋልያዎቹን የግብ ማግባት ዕድል ማምከን ተያይዘዋል። በተቃራኒው ጨዋታው የቀለላቸው የሚመስለው ባለሜዳዎቹ በ30ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በተገኘ ኳስ የኒጀርን ግብ ጎብኝተው ተመልሰዋል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም አማኑኤል ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና ተቆጣጥሮት ለመስዑድ ያቀበለውን ኳስ በሚገርም መግባቦት መስዑድ ለሽመልስ አቀብሎት ሽመልስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በ14ኛው ደቂቃ የተቆጠረባቸውን ጎል በመያዝ አጋማሹን ለማገባደድ የፈለጉ የሚመስሉት ተጋባዦቹ በ39ኛው ደቂቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዋልያው የግብ ክልል ደርሰዋል። በቆመ ኳስ የተገኘውን አጋጣሚም ዩሱፍ ዳውዳ ሳጥን ጫፍ ሆኖ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ተክለማርያም ምንም ሳይቸገር በቀላሉ ይዞበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በተገኘ የመዓዘን ምት ዋልያዎቹ ድንቅ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል። በዚህ ደቂቃ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ ሽመልስ ለመስዑድ አመቻችቶለት መስዑድ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። አጋማሹም በአማኑኤል እና መስዑድ አማካኝነት በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ዋልያዎቹ መሪ ሆነው ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽን በጥሩ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የገቡት ሚዳቆዎቹ በ49ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት ወደ ጎል ደርሰው ነበር። ነገርግን ሙከራቸው ስል ስላልነበር ግብ ሳያስቆጥሩ ተመልሰዋል። በተቃራኒው በአንፃራዊነት ኳስን በኒጀሮች ተነፍገው አጋማሹን የጀመሩት ዋልያዎቹ ሊሰነዘሩባቸው የነበረውን ጫናዎች በመመከት በቶሎ የጨዋታውን የሃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው መልሰዋል። ቀድመው ወደነበሩበት የኳስ ቁጥጥር ከተመለሱ በኋላም በ54ኛው ደቂቃ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረዋል። በዚህም በዛሬው ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ሱሌማን በፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ ተጋጣሚ ክልል ደርሶ ወደ ሳጥን ያሻማው ኳስ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ተረባርበው አውጥተውበታል።

ይህንን የሱሌይማን ድንቅ አጋጣሚ ከተመለከትን ከደቂቃ በኋላም አቡበከር በተንጠልጣይ ያገኘውን ኳስ ተቀብሎ ወደ ጎል የመታው ኳስ ሌላ የዋልያዎቹ አስቆጪ እድል ሆኖ አልፏል። አሁንም የኒጀሮች የግብ ክልል መዳረሻቸውን ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በ59ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ተሻምቶ ጌታነህ በግንባሩ ወደ ጎል በሞከረው ኳስ ሦስተኛ ግብ ለማስቆጠር ታትረዋል። ዒላማውን ስቶ ከወጣው የጌታነህ ሙከራ ከተደረገ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ይህንኑ ሙከራ ያደረገው የቡድኑ አምበል ከተከላካዮች መሐል አምልጦ በመውጣት ያገኘውን ድንቅ ኳስ ግብ ጠባቂው ሞሳ አልዞማ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሚጋመስበት ሰዓትም ኒጀሮች የመከላከል ባህሪ ያለው ተጫዋች በመቀነስ የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች በማስገባት ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። ነገርግን የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደራጀ ስላልነበር እንዳለሙት የጠራ የግብ ማገባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው ቀጥሏል። ዋልያዎቹ በበኩላቸው ኒጀሮች ለማጥቃት ትተውት በሚሄዱት ቦታ ክፈተቶችን እያገኙ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሞክረዋል። በ70ኛው ደቂቃም ኒጀሮች የግብ ክልላቸው አካባቢ ሲቀባበሉ የተሳሳቱትን ኳስ ጌታነህ ከበደ አግኝቶት የሞሳ አልዞማ መረብ ላይ አሳርፎ የዋልያዎቹ መሪነት ወደ ሦስት ከፍ ብሏል።

ሦስተኛው ጎል ከተቆጠረ በኋላ ስታዲየሙ አካባቢ እንደሚነፍሰው ቀዝቃዛ አየር የተቀዛቀዘው ጨዋታው እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ሳይስተናገዱበት ቀጥሏል። አሸናፊ መሆናቸውን እያረጋገጡ የመጡ የመሰለው ዋልያዎቹም የደከሙ የአማካኝ እና የአጥቂ መስመር ተጫዋቾችን በመቀየር ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ ተጫውተዋል። ኒጀሮችም ተስፋ መቁረጥ በጉልህ በሚታይበት እንቅስቃሴ ጨዋታውን ለማገባደድ ችለዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ ተጨማሪ ደቂቃዎች በታዩነት ቅፅበትም ተቀይሮ የገባው ታፈሰ ሰለሞን የመርሐ-ግብሩን የመጨረሻ ሙከራ ሰንዝሮ መክኖበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይታይበት በዳውዱ ዊልያምስ ፊሽካ ተገባዷል።

በተያያዘ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አራተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጨዋታቸውን 1-1 አገባደዋል። ውጤቶቹን ተከትሎም ምድቡን አይቮሪኮስት በ7 ነጥብ ስትመራ በተመሳሳይ ማዳጋስካር 7 ነጥቦችን በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሁለት ጨዋታዎችን ድል የቀናው ዋልያው ደግሞ የምድቡ ግርጌ ላይ የተቀመጠችው ኒጀርን በሦስት ነጥብ በልጦ በስድስት ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!