ተመስገን ዳና ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ጥሪ ቀረበለት

የኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች በሴካፋ ዋንጫ የሚወዳደሩ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንዲይዘው ፌዴሬሽኑ መርጦታል፡፡

በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት የሴካፋ ከ17 ዓመት ውድድር የሚከናወን ሲሆን በውድድሩ ላይም ኢትዮጵያ ተሳታፊ መሆኗ ተረጋግጧል። ለዚህ ብሔራዊ ቡድን በቀጣዮቹ ቀናት ዋና አሰልጣኝ እንደሚሾም የሚጠበቅ ሲሆን ታንዛኒያ ላይ በኅዳር አጋማሽ ለሚደረገው ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ደግሞ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንዲመራው ፌዴሬሽኑ ጥሪ ማቅረቡን ሶከር ኢትዮጵያ ከፌዴሬሽኑ እና አሰልጣኙ ለማረጋገጥ ችላለች፡፡

በሀዋሳ ከተማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው አሰልጣኙ በ2010 ዩጋንዳ ላይ በተዘጋጀው የሴካፋ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን እስከ ፍፃሜው ይዞ በመጓዝ አስደናቂ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በ2011 በሀዋሳ ከተማ የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ረዳት በመሆን ከሰራ በኋላ በ2012 የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ደቡብ ፖሊስን ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!