የደጋፊዎች ገፅ | ቆይታ ከሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ግሩም ባሻዬ ጋር

ብዙ እግርኳሰኛ ትውልዶችን መፍጠር የቻለው ፣ በበርካቶች ዘንድ ከሚወደደው እና ከሚደገፈው የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ከሆነው ከግሩም ባሻዬ ጋር የተደረገ ቆይታ።

እግርኳስን ከልጅነት እስከ ዕውቀት ተጫውቷል። ሀዋሳ ሞቢል ሠፈር የተወለደው የዛሬው የደጋፊዎች ገፅ ዕንግዳችን የቀድሞው ተጫዋች ግሩም ባሻዬ ይባላል። በፕሮጀክት መጫወት ጅማሬውን አድርጎ በአየር መንገድ፣ ሙገር፣ መድን፣ ደቡብ ፖሊስ፣ አዳማ ከተማ፣ ኒያላ እና ደደቢት ክለቦች የእግርኳስ ዘመኑን አሳልፏል። እግርኳስን ካቆመ በኃላ ወደ ንግዱ ዓለም በመግባት መንቀሳቀስ የጀመረው ግሩም በመልካም ስብዕናው እና ለተቸገረ በመርዳት በበጎ ተግባሩ ብዙዎች ያከብሩታል፣ ይመሰክሩለታልም። የሚወደው ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ አለው ከተባለ ከሜዳ የማይርቀው ግሩም ዘውትር ስለ ሀዋሳ ያወራል፣ ይቆረቆራል፣ ይቆጫል። ታዲያ ይህን ያወቁ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በ2009 የክለቡ የደጋፊ ማኅበር ፕሬዝደንት አድርገው ሾመውታል። ያለፉትን አራት ዓመታት በክለቡ የቦርድ አባል በመሆን ደጋፊውን ለማብዛት ፣ ክለቡ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው እና ሀዋሳ የራሱ ቀለም ያለው ቡድን እንዲሆን ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የቀድሞ ተጫዋች የዛሬው የደጋፊ ማኅበር ፕሬዝደንት ግሩም ባሻዬ በደጋፊ ማህበር ፕሬዝደንትነት ሀዋሳ ከተማን በመወከል በደጋፊዎች ገፅ አምዳችን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ትውልድህ እና የእግርኳስ አጀማመርህን ጫማ እስከሰቀልክበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት በዝርዝር አጫውተኝ እና በማስከተል ወደ ዋናው ጥያቄዬ አመራለሁ።

ሀዋሳ ሞቢል ሠፈር ነው ተወልጄ ያደግኩት። ለፕሮጀክት ውድድር ደቡብን ወክዬ ደብረ ማርቆስ ከተማ በ1992 ላይ በተካሄደው ውድድር ልዩ ተሸላሚ ሆኜ  ከዚያ በኋላ 1994 ላይ በክፍሌ ቦልተና ይሰለጥን በነበረው የአየር መንገድ ቢ ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካተትኩ። በመቀጠል ከ1995/96 ድረስ ለሀዋሳ ቢ ቡድን ተጫወትኩ። ከዚያም ከ1997/98 ደቡብ ፖሊስ ብሔራዊ ሊጉ እያለ ኮኮብ ተጫዋች ተሸልሜ ወደ ኢትዮጵያ መድን በፊርማ ክፍያ ወሰደኝ። መድን የሄድኩት 1999 ላይ ነበር። በመድን በስዩም አባተ ስር ለሁለት ዓመት መሰልጠኔ በጣም ደስ ብሎኛል። በጣም ስኬታማ እና የማይቆጨኝ ጊዜ አሳልፌ ከዚያ ደደቢት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት በወቅቱ ከፍተኛ በሆነ ገንዘብ አስፈረመኝ። ደደቢት በመጣሁበት ዓመት የቡድኑ አምበል አደረጎኝ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል። በመቀጠል ያመራሁት በሞሪኒሆ ይሰለጥን ወደነበረው አዳማ ከተማ ነበር። ያኔም ከፍተኛ በሚባል ገንዘብ ተዘዋውሬ አንድ ዓመት ከምናምን ከተጫወትኩ በኋላ ባለመግባባት ለቅቄ ኒያላ ገባሁኝ። በኒያላም ሁለት ዓመት ከቆየሁኝ በኋላ በሙገር ከጋሽ ግርማ ስብስብ ውስጥ ሆኜ ላለመውረድ በሚጫወትበት ሰዓት የመጨረሻ ጨዋታዬን አዲስ አበባ ስታዲየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 2004 ላይ አድርጌ ጫማዬን ሰቀልኩ።

እንዴት ነው ወደ ሀዋሳ ደጋፊ ማኅበር የሄድከው ?

እግርኳሱን ካቆምኩ በኃላ ወደ ዱባይ ሄጄ የስፖርት ትጥቅ ለራሴ ገዝቼ ልመጣ ሳስብ ዕቃውን አምጥቼ እዚህ ብሸጠው አዋጭ ነው ብዬ በማሰብ የስፖርት ትጥቅ ነጋዴ ሆንኩኝ። አስቀድሞ ጀርመን ሀገር የመሄድ ሀሳብ ቢኖረኝም ይህን ትቼ ዱባይ እየተመላለስኩ በስፖርት ትጥቅ ንግድ ውስጥ በመግባት መስራት ጀመርኩ። እኔ ባደግኩበት ክለብ እየተረዳሁ ስላደግኩ ከዚያ ካተረፍኩት ነገር በክፍለ ከተሞች፣ በቀበሌዎች፣ በታዳጊዎች፣ በብሔራዊ ሊግ ላይ ታዳጊዎችን መርዳት እንዳለብኝ በማመንም የበኩሌን አደርጋለሁ። ራዳሁ ብዬ ለማውራት ሳይሆን መርዳት እኔን ስለሚያስደስተኝ ነበር። ወደ ጥያቄህ ስመጣ ሀዋሳ ላይ የአሰልጣኝ ቅጥር ፣ የኮሚቴዎች ያለአግባብ ውሳኔዎችን ሳያቸው የግድ ወደዚህ ነገር መግባት አለብኝ ብዬ አስብ ነበር። ከዚያም በሀዋሳ ደጋፊዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሳልገኝ ፕሬዝደንት አድርገው መረጡኝ። ከዚያም ‘የደጋፊ ማኅበር ብቻ መሆኑን አልቀበልም ፤ የቦርድ አባል ሆኜ የሚወሰኑት ውሳኔዎች ውስጥ እጄ የሚኖርበት ከሆነ ነው የምቀበለው’ ብዬ ነው አባል የሆንኩት። በሀዋሳ ከተማ አሁን አስተውለህ ካየኸው 5 ተጫዋች ማሳደግ ግዴታ ነው። እያንዳንዱ የሚመጣው አሰልጣኝ ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ዘንድሮ ላይ እዳየኸው ሀዋሳ ከተማ 10 ወይም 15 ተጫዋች የሚያስፈርም ክለብ አይደለም። ይህንን ነገር ያስቆምነው አሰልጣኞችን ላላስፈላጊ ሙስና እንዳይጋለጡ ነው። ይህን ደግሞ ያደረግነው እንደቦርድ አባል የህዝብ ኃላፊነት ስላለብን እና የህዝብን ገንዘብ መጠበቅ ስለሚያስፈልግ ነው።

የደጋፊ ማኅበሩ አደረጃጀት እና አወቃቀሩ እንዴት ነው ?

ማኅበሩ ፕሬዝዳንት እና ሰባት የሥራ አስፈፃሚዎች አሉት። ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ ሂሳብ ሹም ፣ ንብረት ክፍል እያለ ሰባት ሥራ አስፈፃሚዎች አሉትነው።

ሀዋሳ በሜዳው ብቻ ነው በደጋፊ የሚታይ የነበረው ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይነስም ይብዛም በሌሎች ሜዳዎች ላይ ደጋፊው ይታያል፤ ያንን እንዴት ማምጣት ቻላችሁ ?

ይህ የእኛ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነው። አሁን እንዳየኸው በሦስት ዓመት ውስጥ በነበሩ ሒደቶች መድረስ የሚገባንን ያህል ባንደርስም መጀመሪያ ክለቡ የራሱ የሆነ ሎጎ ፣ ቅርፅ ፣ የሆነ ቀለም እንዲኖረው አድርገናል። ሀዋሳ አንጋፋ እና ግንባር ቀደም እንደ መሆኑ መጠን የደጋፊው ቁጥር በዛው መጠን ያልበዛበት ምክንያት ደግሞ ከጊዜያት በኋላ የመጡት የክለቦች አደረጃጀት ዘርን ይዞ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ጠንካራ ጎንም ጎጂ ጎንም አለው። ሀዋሳን እንደ ክለብ ስታየው ተጫዋች በማፍራት እና በውስጡ ባለው አደረጃጀት ብቸኛ ክለብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ምናልባት መብራት ኃይል ነው ሊስተካከለው የሚችለው ፤ 425 ስፖርተኞች አሉት። የደጋፊው ቁጥር ሳይሆን መታየት ያለበት ክለቡ ውስጥ ያለው ዘርፉ ነው። በአትሌቲክስ ፣ ቅርጫትኳስ ፣ እግርኳስ በሴቶችም በወንዶችም ቡድኖች አሉት። በታዳጊ ከ20 ዓመት እና 17 ዓመት እያለ ወደ ታች የሚወርድ አደረጃጀት አለው ፤ 425 ስፖርተኛ ያለው ብቸኛ ክለብ ነው። ያም የደጋፊ ማህበሩ ውጤት ነው። ደጋፊውም ወደ ተለያዩ ክልሎች በመጓዝ እንዲደግፍ ስፖንስር በመፈለግ በነፃ ወደ ክልል ሜዳዎች ሄዶ እንዲደግፍ አድርገናል ፤ ቁጥሩም እንዲጨምር ረድቶናል። ደጋፊውም ተባብሮ ተጫዋቾችን ‘አለን ከጎናችሁ ነን’ በማለት ኢንሴቲቭ ሲከፍል የነበረም ነው። በዚህ ደግሞ ብቸኛው የደጋፊ ማኅበር ነው።

የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ሀዋሳ ከተማን እንደክለብ ተፈታትኖታል ?

ኢትዮጵያ ውስጥ ሀዋሳ ከተማ ብቻ አይደለም ሌሎች ክለቦችንም ጨምሬ ልንገርህ። ክለቦች ከመንግስት ትክሻ ላይ ካልወረዱ እና ወደ ህዝባዊነት ካልመጡ በስተቀር አደጋ ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ሰፊ ነው። ትልቁ ሞዴላችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው ፤ በባለሀብቶች ነው የሚደገፍው። የመንግስት ክለቦችን ካየሀቸው ሜዳቸው ላይ በቂ መቀመጫ ኖሮ ደጋፊውን ማምጣት አለባቸው። ደጋፊውን ስታመጣ ደግሞ በስፖንሰር የሚገኙ ነገሮችን ግንዛቤ ሰጥተህ ህዝባዊ ምታደርግበት ነገር ሊመጣ ይችላል። የትኛውም ዓለም ላይ ብትሄድ 90% ገቢያቸው ከስፖንሰር የሚገኝ ነው። ስፖንሰር ደግሞ የምታደርገው ከባለሀብት እና ከህዝቡ ነው። ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት እስከ ቀበሌ ከመንግስት ትክሻ ላይ እንዲላቀቅ ፍቃደኛ የሆነ አሰራር ስለሌለ ሀዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በርካታ ክለቦች አደጋ ላይ ናቸው ።

የሲዳማ ቡና ከይርጋለም መምጣት እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ በሲዳማ ክልል መጠቃለሏ እንደ ክለብ የሚያመጣው ስጋት አለ ?

ይሄ ስጋት ተቀባይነት የለውም። ሁለቱም የሚተዳደሩት ራሳቸውን በቻሉ የከተማ አስተዳደሮች ነው። ሲዳማ ቡና አሰራሩን ህዝባዊ አድርጎት ከባለሃብቶች እና ከቡና ድርጅቶች የሚያገኘው ገንዘብ አለው። ሀዋሳ ከተማ ግን ከህዝብ ከሚሰበሰብ የመንግስት ገንዘብ በሚገኝ ባጀት ነው ሙሉ በሙሉ የሚተዳደረው። ይህን አሰራሩን ቀርፎ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ መፍጠር ከተቻለ ነገ ከነገ ወዲያ ይፈርሳል የሚለው ነገር አይኖርም። በአንድ ክልል ሁለት ክለብ ስለመጣ ይቸገራል ማለት ግን አይደለም። ነገር ግን ከመንግስት አደረጃጀት ወጥተህ የምትሰራ ከሆነ ለምን ስድስት እና ሰባት ክለብ አይኖርም ? አዲስ አበባ ከተማ ላይ እኮ 11 ክለቦች ነበሩ ፕሪምየር ሊግ የሚወዳደሩት። ግን ሁሉም የመንግስትን ካዝና የሚጠብቅ ከሆነ እንደምታየው ድርቀት ይመጣና ሁለት ክለብ ምናምን ፕሪምየር ሊግ ላይ ይቀራል። ስለዚህ ይሄንን ስጋት አልቀበለውም።

ሀዋሳ ከተማን ለበርካታ ዓመታት ተመልክተኸዋል። በሀዋሳ ደስተኛ የሆንክበት የምታስታውሰው ጨዋታ አለ ?

በጣም ደስተኛ የሆንኩት ውበቱ አባተ ሀዋሳን እያሰለጠነ ቅዱስ ጊዮርጊስን 4-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ነው። ያንን ለምን አልክ ካልከኝ ታቅዶበት ፣ ተስርቶበት የተገኘ ውጤት እንደሆነ በመገንዘቤ ነው። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አራት ዓመት ላለመውረድ ነው የተጫወተው ፤ ለእኔ ግን ምርጡ ሂደት ያኔ ነው። ምክንያቱም እግርኳስ በሂደት የሚገነባ ነገር ነው። እኔ በነበርኩበት ወቅት እና ከዛ በፊት ሀዋሳ ከተማ አሰልጣኞችን አሰናብቶ አያውቅም። ፍሰቱን ሂደቱን የሚያይበት መንገድ ስለነበረው አሰልጣኞች በራሳቸው ካልለቀቁ አሰናብቶ አያውቅም ነበር። ከስምንት ዓመት ወዲህ በውበቱ አባተ የነበሩት ጊዚያቶች ምርጥ ጊዜያቶች ናቸው ።

በሀዋሳ ከተማ ያዘንክበት ቀንስ መቼ ነው ?

ምን አለ መሰለህ ያመራር ክፍተት ስለነበር ፌደሬሽኖች እንደልባቸው የሚያደርጉበት አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ ሜዳህ ላይ ያለ በቂ ማስራጀ ‘ክለቡ ረብሿል’ በሚል አግባብ ያልሆነ ቅጣት ይጣልብሃል። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት ካስታወስክ አሳላ ላይ ተጫወት ተባለ። አሰላ ግማሽ ተጫወትን ከዛ ከአሰላ አዳማ ተባለ። እንደገና ደብረዘይት መከላከያ ኮሌጅ ያለ ደጋፊ ተጫወትን። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ግን ገብተው ጭራሹን የተጫዋቾችን ሰርቪስ ተደበደበ። እንደገና ደግሞ ጥፋተኛ ሀዋሳ የተባለበት ቀን አዝኛለሁ ፤ በአሰራሩ ማለት ነው። እንደቦርድ እና ደጋፊ ማህበርነቴ ፌደሬሽን መጥቼ ስጠይቅ ፤ ሁሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚረብሽ ነገር ጥያቄ ጠይቀህ መልስ ማታገኝበት እና እንደ አስፈላጊነቱ ብለው የሚያስገቡት የህግ ማሰሪያ አለ። እንዳስፈላጊነቱ ማለት አንተ ለወደድከው እና ለፈለግከው ነገር ህግን እየጠመዘዝክ ማስቀመጥ ትችላለህ ማለት ነው። ያዛን ጊዜ ደጋፊውም ክለቤም የተጉላላበት ጊዜ ስለሆነ በጣም ያዘንኩበት ቀን ነው ።

የሀዋሳ ደጋፊ ምንድነው ልዩ የሚያደርገው ነገር ?

በውበቱ ጊዜ እንደገነገርኩህ ጊዮርጊስን እንዳሸነፈ ሁሉ በመከላከያ 4 -1 ሲሸነፍ ደጋፊው ቆሞ ነው ያጨበጨበው። ሀዋሳ ከተማን ለየት የሚያደርገው ሁሌም ትሪቡን ላይ ለተቃራኒ ቡድን ደጋፊ ቦታ ይሰጣል። እግርኳስ ወዳጅነት ነው። ያንተ መሸነፍ አለመሸነፍ ጉዳይ ሳይሆን እግርኳስ የተመሰረተበትን ወዳጅነትን አንድነትን ነው እንግዳ ተቀባይነትን እንጂ ሌላ አይደለም። ለምሳሌ ከጎንደር ድረስ የመጣውን ደጋፊ ከአንግል ጀርባ ቦታ በመስጠት ልታሸንፍ የምታደርው ነገር በእኔ አመራር ዘመን በፍፁም የማልቀበለው ነው። ሁለተኛ እንደ ማንኛውም ደጋፊ በዜማ እና በግጥም የሚፉጋገሩትም ነገር እደግፈለሁ። ከዛ የዘለለ ዘርን ፣ ማንነት እና ስብዕና የሚናካ ነገር ግን እኛ ጋር የለም። ሀዋሳ ከተማ በዘር የተደገፈ ክለብ አይደለም። በዚህ የተጎዳበት ጎን አለ ፤ የተጠቀመበት ጎንም አለ። በዘር ባለመደገፉ ደስ ይለናል። አሁን ድሬድዋ ፣ አዳማ እና ሀዋሳ ከተማን ካየህ ለምንድነው ቁጥራችን ያነሰው ? ከተባለ በዘር ስላልተደገፍን ነው።

በእግርኳስ ውስጥ የገባው በዘር የመደገፍ አካሄድ ያሳስብሀል ማለት ነው?

በሚገባ ! በዚህ ሦስት አራት ዓመት ውስጥ ለቻምፒዮንነት የሚጫወቱ ክለቦች እንደ ሀዋሳ ከተማ ብቃት ኖሯቸው ልጅ አሳድገው ይመስልሃል ጠንካራ ቡድን የሆኑት ? አይደለም። የደጋፊያቸው ቁጥር የበዛው ስፖርቱን ወደውት ፣ የኳሱ ፍሰት በትክክል ማርኳቸው ነው ? አይደለም። ለቻንፒዮንነት የሚጫወቱ ክለቦች ስናያቸው በዘር ስያሜ የነበሩ ናቸው። በሜዳቸው የሚያደጉት ጨዋታ ጫናው ከባድ ነው። በበጥቅሉ በጣም ጥሩ ቢሆንም በዚህ ረገድ ግን እኔን አሁን የሚያሳስበኝ ጨዋታዎች በቲቪ መታየታቸው ነው። ፌደሬሽኑ ይህንን ነገር ሰርቶበት ካልወጣ በአደባባይ ልንዋረድበት የምንችልበት መንገድ ሊኖር እንደሚችል ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ጨዋታዎቹ ዓለም ላይ ይለቀቃሉ። እስካሁን የመጣንበት አላስፈላጊ መንገድ ካልተቀረፈ ጥሩውንም መጥፎውንም ነገር ዓለም በቀጥታ ስርጭት የሚመለከተው ስለሆነ እዚህ ላይ መሥራት አለበት።

ሊጉ በቅርቡ ይጀመራል ፤ በዝግ ስታዲየም ነው ሚከናወነውም። ሀዋሳ ከተማ ከደጋፊ ማግኘት ያለበትን ጥቅም የሚያጣ ይመስልሀል ? ለዛስ ምን መፍትሄ አላችሁ ?

ያው እንደሀገር የመጣ ነገር ስለሆነ የምትቀበለው ነገር ነው። በክለቡ ግን እንደ ደጋፊ ቁጥራችን ትንሽ ነው። በፍላጎት እንደግፍ እንጂ መጀመሪያም በገንዘብ የሚደገፈው በቦርድ አባላት በሚደረግ ድጋፍ ነው። ህዝባዊ መሆን ግን ይቀረናል። ደጋፊው ምን ሊያደርግ ይችላል ? እንዴት ሊያይ ይችላል ? የሚለውን ነገር እስካልተፈቀደልን ድረስ ምንም ማድረግ አንችልም። እስከሚፈቀድልን ድረስ በቴሌቭዥን እንከታተላለን። እንደ ደጋፊነት ከስፖርቱ በዘለለ ወደ ሜዳ ለመምጣት ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን ለህብረተሰቡ የሚደረገውን የግንዛቤ መስጨበጫ ከመንግስት ጎን ምክር ለመስጠት ከፍተኛ አስተኦፆ የሚያደርገው ደጋፊ ማህበሩ ነው ። ደጋፊው ወደ ሜዳ ባለመግባቱ ገቢ ልናጣ እንችላለን ፣ ተፅእኖ ያደርግብናል ግን ተምረንበት እንመጣለን። አሁንም እኛ በመንግስት እየተደገፍን ነው። ምንም መወሻሸት አያስፈልግም ፤ ክለቡ ህዝባዊ መሆን አለበት። ሌላ ዓለም ላይ ካየህ በመለያ ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ። ዛሬ በአንድ ሰው ካልጀመርን ነገ እነሱ ላይ አንደርስም። ክለቦችም የፋይናስ አቅማቸውን የሚያጠናክሩበት ሥራ መስራት አለባቸው እላለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!