ለብዙዎች አርዓያ መሆን የሚችለው የአሰልጣኝ ህይወት አረፋይነ የእግርኳስ ጉዞ ፣ የህይወት ተሞክሮ እና የወደፊት ህልም በሴቶች ገፅ መሰናዷችን እንዲህ ተቃኝቷል።
በሴቶች እግር ኳስ ለበርካታ ዓመታት ከቆዩት አንዷ ናት። ዕድሜዋ ከአስራዎቹ ሳይሻገር በ1993 በከተማ ደረጃ እግርኳስን መጫወት ከጀመረች አንስቶ መቐለ 70 እንደርታን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ እስካሰለጠነችበት የመጨረሻው የውድድር ዓመት ድረስ ድፍን ሃያ ዓመታትን በስፖርቱ ውስጥ ቆይታለች። በከተማው እና በክልሉ የሴቶች እግርኳስ ሲነሳ ስሟ አብሮ እስከመነሳት ድረስ የደረሰበትን ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተችው ህይወት በወቅቱ የሴቶች እግር ኳስ ክለቦች ባለመኖራቸው በክለብ ደረጃ ባትጫወትም ጥሩ ክህሎት ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዷ እንደነበረች ብዙዎች ይመሰክራሉ።
በመቐለ 06 ቀበሌ የተወለደችው ህይወት የቤተሰቡ ብቸኛ ሴት ልጅ ሆና በወንዶች ተከባ ብታድግም ልቧ ለእግር ኳስ በማድላቱ በቤተሰብም ሆነ በሰፈር ውስጥ የደረሰባት ጫና አልነበረም። 1993 ላይ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለች በትግራይ ልማት ማሕበር (TDA) ስር በነበረው የሴቶች እግር ኳስ ፕሮጀክት መስራት ጀምራ በዞን እና በክልል ደረጃ በበርካታ ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ ቆይታ በ1997 ወደ ዩንቨርስቲ ከገባች በኃላ ደግሞ በሦስት የዩንቨርስቲ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች። በተለይም ተመራቂ ተማሪ ሆና በተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት የውድድሩን ዋንጫ እና ኮከብ አሰልጣኝ ሽልማቶች ያሸነፈችበት ጊዜ የወቅቱ ትልቁ ስኬቷ ነበር።
በባህሪዋ ቁጡ እና ቆፍጣና መሪ እንደሆነች በብዙዎች የሚነገርላት ህይወት በትምህርት ላይ ያላት ፍላጎት እና በወጣት ተጫዋቾች ላይ ያላት ፅኑ አቋም ጠንካራ ጎኖቿ እንደሆኑ ከሷ ጋር በቅርበት የሰሩ የሚመሰክሩት ሃቅ ነው። በዚህ መንገድ የተቃኘው የአሰልጣኝነት ህይወቷ ታድያ የጀመረው በዶክተር አባይነህ እገዛ የዩኒቨርስቲውን ቡድን ይዛ ጥሩ ውጤት ባስመዘገበችበት ወቅት ነበር። የስፖርት ሳይንስ ድግሪዋን ይዛ ወጥታ በመምህርነት ሙያ ስድስት ወራትን ካገለገለች በኋላም ግን የእግርኳስ ፍቅሯ ዳግም ወደ ስፖርቱ መልሷታል።
የስፖርት ሳይንስ ምሩቅ መሆኗ እና ቀደም ብላ የአሰልጣኝነት ኮርሶች መውሰዷን በማስተዋል የሙያው አርዓያዋ አሰልጣኝ ምስግና ካሕሳይ አስፈላጊውን ነገር በማሟላት ወደ አሰልጣኝነቱ እንድትመለስ አድርጓታል። በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሲሳይም (ም/ኮማንደር) እገዛ እየተደረገላት በተማሪነቷ ጊዜ ወደጀመረችው ሙያ በጥልቀት መጓዝ ጀመረች።
በአሰልጣኝነት ኮርሶች ዙሪያ የህይወት ተሞክሮ ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው። የመጀመርያ እና ሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ሥልጠናዎችን በ1998 እና 1999 ዩንቨርስቲ እያለች ነበር የወሰደችው። በሚሊኒየሙ ደግሞ በሴቶች እግርኳስ አሰልጣኝነት ዘርፍ ደቡብ አፍሪካ ላይ ተማረች። በወቅቱ ይህን ሥልጠና ከኢትዮጵያ እሷ እና መሰረት ማኔ ነበሩ የወሰዱት። በዚህ አጀማመሯ በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ከ’ሲ’ ጀምራ እስከ ኢንስትራክተርነት በራሷ ወጪ ስትማር ቆይታለች። 2008 ላይ ደግሞ ወደ ካሜሩን አምርታ ሦስት ዓመት ቀደም ብላ በሀገር ደረጃ ያሳካችውን የኢንስትራክተርነት ማዕረግ ወደ ካፍ ኢንስትራክተርነት ከፍ አድርጋለች።
በእስካሁኑ የእግርኳስ አሰልጣኝነት ህይወቷ መቐለ 70 እንደርታን ስታሰለጥን ከዚያ በፊት ግን በፕሮጀክት ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ ስትሰራ ቆይታለች። እዚህ ላይ ህይወት ከክለብ አሰልጣኝነት ይልቅ ታዳጊዎች ላይ መስራት ከባድ ስለመሆኑ አበክራ ትናገራለች። “በክለብ ደረጃ ያለቀላቸው ተጫዋቾች ይዘህ ነው ቡድን የምትሰራው። በፕሮጀክት ግን ተጫዋች ነው የምትቀርፀው። ታች ያለው ስራ ትንሽ ፈታኝ ስለሆነ ብቁ ባለሞያዎች ብቻ መስራት አለባቸው። በተለይም በሴት እግርኳስ ፕሮጀክት ላይ ያሉት ፈተናዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ሴት ልጁን በቀላሉ ወደ ፕሮጀክት የሚልክ የለም። ቤት ድረስ ሄደን ነበር የምናሳምናቸው። በጀትም የለም ፤ የሴት እግር ኳሱም ብዙ ትኩረት የለውም። ለዛም ነው ወደ ክለብ እግርኳስ ስመጣ ብዙም ያልከበደኝ። በመጀመርያው ዓመት ልምድ የሌላቸው የአከባቢያችን ልጆችን ይዘን ነው ጥሩ ውጤት ያመጣነው። ቡድናችን በታዳጊዎች ላይ የተመሰረተ ነበር። በሁለተኛው ዓመት የፕሪምየር ሊግ ቆይታችን ግን ትንሽ የልምድ ችግር ነበረብን።”
ስህተቶቿን አጋኖ ለማሳየት ከሚሞክሩ ሰዎች ጀምሮ የአሰልጣኝነት ህይወቷ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የምትናገረው ህይወት የሌሎች አዳዲስ ወደሙያው የሚገቡ ሴቶችን ተነሳሽነት ላለመቀነስ ስትል ችግሮቹን አብዝቶ ማውራትን አትደግፈውም። በመምህርነት ደመወዟ ሥልጠናዎችን በምትፈልገው መጠን ለማግኘት ተቸግራ የነበረ ቢሆንም ብቸኛ እና ብርቅዬ እህታቸው በመሆኗም ይመስላል የወንድሞቿ ድጋፍ ሳይለያት ያሙያ ፈተናዎችን እያለፈች ዛሬ ላይ ደርሳለች።
በሥልጠናው መንገድ ውስጥ ለመግባት ፈተናዎች ይብዙባት እንጂ የትዳር ህይወቷ መንገዶች እንዲቀሉላት አድርጓል። በራሳቸው ሰፊ ትኩረትን የሚሹት ትዳር እና እግርኳስን አብሮ ማስኬድ ከባድ ቢሆንም ለእንስቷ አሰልጣኝ ግን የጥንካሬ ምንጭ ሆኗታል። “ዋናው ቁልፉ ነገር የትዳር አጋር አመራረጥ ነው ፤ ሙያህን የሚወድ እና የሚደግፍ የትዳር አጋር ካለህ ሁለቱን አብሮ ማስኬድ ያን ያህል ከባድ አይደለም። ባለቤቴ ሠለሞን ብርሃነም እንደዛ ዓይነት ሰው ነው። መምህርም ስለሆነ በሁሉም ረገር ይደግፈኛል። ከመጀመርያው ፍላጎቴን ስለሚያውቅ ብዙ ነገርም አግዞኛል። እሱ ባይኖር እኔ እዚህ ቦታ ላይ አልገኝም ነበር። ካሜሩን ለሥልጠና ስሄድ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ህፃን ትቼለት ነው የሄድኩት። ብቻህን አንድ ዓመት ከስድስት ወር ህፃን ማቆየት ከባድ ነው ያውም ወንድ ሆኖ ፤ ይህን ያህል ነው ያገዘኝ እና መስዋዕትነት የከፈለልኝ።” የሚለው አስተያየቷም ትዳር እና እግርኳስን ማስኬድ የሚቻል ስለመሆኑ ምስክር ነው።
ከትዳር ውጪ ወደ ተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ሙያ የሙመጡ ሴቶች በበርካታ ነገሮች የሚፈተኑ ቢሆንም ህይወት ግን ከራሷ ልምድ በመነሳት መስዕዋትነት እና ትምህርት ዋነኛ መፍትሄዎች ስለመሆናቸው በዚህ መንገድ ላይ ላሉ ሁሉ ቀጣዩን ቁም ነገር ታስተላልፋለች። “መጀመርያ ከባድ መስዋዕትነት እንደሚፈልግ አውቀው ራሳቸውን ብቁ ማድረግ አለባቸው። ሁሉም ትልቅ ደረጃ ላይ ያለ ሰው ዘው ብሎ አይደለም ስኬታማ የሆነው ፤ ፈተናዎች አሉ። ለእነሱም በቂ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው። አሁን እኔ 1993 ላይ ነው እግር ኳስን የጀመርኩት በሙያው ደመወዝ ማግኘት የጀመርኩት ግን 2011 ላይ ነው።
ለአስራ ስምንት ዓመታት በእግርኳስ ደመወዝ አግኝቼ አላውቅም ፤ መስዋዕትነቱ ይህን ያህል ነው። በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም ፈተናዎች አሉ በፈተናዎቹ ሳይበገሩ ያሰቡትን ደረጃ መድረስ ግን ይችላሉ። በእግርኳስ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሙያ መሰናክል ያለ ነገር ነው። ሌላው ደግሞ ትምህርት ወሳኝ ነው ፤ በተለይም አሰልጣኝነት ትምህርት ፣ ማንበብ እና ራስን ማሳደግን ይጠይቃል። በኢትዮጵያ ደረጃ እግርኳሳችን እየወረደ ነው። ተጫዋች ጠፍቶ አይደለም ፤ ችግሩ ሥልጠናው ነው። የሦልጠና መንገዳችን ትክክል አይደለም ፤ ሳይንሳዊም አይደለም። እና ይህን ነገር ለመቀየር መማር ፣ ማንበብ ፣ ራሳችንን ለመቀየር ጥረት ማድረግ አለብን። እኔ ስለተማርኩ ነው የተቀየርኩት ፤ መማሬ ውጤታማ አድርጎኛል።”
አሰልጣኝ ህይወት ዓረፋይነ ከእስካሀኑ ጉዞዋ በላይ የወደፊት ህልሟ ሰፊ ሆኖ ይታያል። “የሴቶች ብሔራዊ ቡድኑ የማሰልጠን ዕቅድ አለኝ። ከአሁኑ የበለጠ ልምድ አግኝቼ በትምህርትም ራሴን አሻሽዬ ወደ ወንዶች እግርኳስ መግባትም እፈልጋለሁ። በወንዶች እግርኳስ የራሴን አሻራ የማሳረፍ ዕቅድ አለኝ። ሴት ዕድል ከተሰጣት ምንም ነገር መስራት እንደምትችል ማሳየት እፈልጋለው። በትግራይ የሴቶች እግርኳስ ገና ነው ፥ አላደገም። ብዙ ሴት የእግርኳስ ባለሞያዎችም የሉም። እኔ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሼ ለሁለም አርዓያ መሆን እፈልጋለሁ። ከዚያ ውጪም የይቻላል መንፈስ እንዲሰርፅ የበኩሌን መወጣትም አንዱ ዕቅዴ ነው። አሁንም በምችለው አቅም የበኩሌን ድርሻ እየተወጣሁ ነው። ከእግዚአብሔር ፍቃድ ጋር አሳካዋለው።” በማለት ዕቅዶቿን ያብራራችበት መንገድም ከፊቷ ረጅም የአሰልጣኝነት ዘመንን እንደምታልም የሚያሳይ ነው።
የወቅቱ የመቐለ 70 እንደርታ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ህይወት ዓረፋይነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራት ቆይታ የህይወት እና የሙያ ጉዞዋን አካፍላን በመጨረሻም ቆይታችንን ከጎኗ ለነበሩትን ሁሉ ምስጋና በማቅረብ አጠናቃለች። “ከፈጣሪ ቀጥሎ ብዙ ማመስገን የምፈልጋቸው ሰዎች አሉ። ቤተሰቦቼ በልጅነት ከወንዶች ጋር ስጫወት ከመፍቀድ እና ከማበረታት ጀምሮ ለእኔ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው አስተምረውኛል። ወንድሞቼን በተለይም ዓለሙ አረፋይነን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። በመቀጠል የትግራይ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽኖችን ማመስገን እፈልጋለሁ። በተለይም ደግሞ አቶ መኮንን ኩሩ በጣም በጣም ብዙ ነገር አግዞኛል። የመቐለ 70 እንደርታ እግርኳስ ክለብ አመራሮችንም ማመስገን እፈልጋለሁ። በተለይም አቶ ሽፈራው ተክለሃይማኖትን ማመስገን እፈልጋለሁ። የሴቶች ቡድናችን ከተመሰረተ ጀምሮ በሁሉም ጉዳይ ለሰከንድም ከጎናችን ተለይቶ አያውቅም።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!