በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሳምንት

ጣልያን
ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአታላንታ ንብረት የሆነው እና በዓመቱ መጀመርያ ላይ ወደ ሴሪ ሲ ክለብ ሞኖፖሊ 1966 ያመራው አማካዩ ኢዮብ ዛምባታሮ ክለቡ በቪርቱስ ፍራንሳቪላ በተሸነፈበት ጨዋታ በሃያ ስምንተኛው ደቂቃ ለአዲሱ ክለቡ የመጀመርያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል።

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ሞኖፖሊዎች በኢዮብ ጎል መምራት ቢችሉም እንግዶቹ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች ሦስት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።

ወደ ክለቡ ከተቀላቀለ ጀምሮ ባለፈው ሳምንት ብቻ ቡድኑ ከኮሴንዛ ካልችዬ ሲጫወት በተቀያሬ ወንበር የተቀመጠው ይህ ወጣት አማካይ በክለቡ ቆይታው ከአንድ ጨዋታ ውጭ በሁሉም በቋሚነት ተሰልፏል።

እንግሊዝ

በሊቨርፑል ከ18 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አማካይ መልካሙ ፍራውንዶርፍ በጥሩ ብቃቱ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት ክለቡ ኤቨርተንን አራት ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ አንድ ግብ ያስቆጠረው አማካዩ ትናንት ደግሞ ክለቡ ሊቨርፑል ኒውካስትልን አራት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ ሞርቶን የተባለ ተጫዋች ላስቆጠራት ግብ አመቻችቶ አቀብሏል።

በክረምቱ የጀርመኑ ሆፈንሄይምን ለቆ ወደ መርሲሳይዱ ክለብ የተዘዋወረው መልካሙ ከወዲሁ የቀያዮቹን ደጋፊዎች ትኩረት ስቧል።

ግብፅ

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የሚገኙት አጥቂው ኡመድ ኡክሪ እና አማካዩ ሸመልስ በቀለ ሀሙስ በተደረጉት የመጨረሻ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ቡድናቸውን ማገልገል አልቻሉም። የአስዋኑ ዑመድ ኡክሪ ከቀድሞ ክለቡ አል ኢትሃድ አሌክሳንደርያ ጋር በነበረው ጨዋታ በተቀያሪ ወንበር ሆኖ ጨዋታውን ሲያጠናቅቅ ትናንት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመረው ሽመልስ በቀለም በተመሳሳይ ክለቡ ከስሞሃ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ተቀያሪ ላይ ሆኖ ጨዋታውን ጨርሷል። በስዊድን የሚገኘው ቢንያም በላይም በተመሳሳይ በዚህ ሳምንት ጨዋታ ማድረግ አልቻለም።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!