ቅዳሜን ለሀገሬ አርሶ አደር – የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች መልካም ተግባር

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና አርሶ አደሩን ለመታደግ በትናንትናው ዕለት በሁለት አካባቢዎች ዘመቻ አደረጉ።

“ቅዳሜን ለሀገሬ አርሶ አደር” በሚል መሪ ቃል በርከት ያሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በትናትናው ዕለት አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድዓ ወረዳ በመጓዝ በአንበጣ መንጋ ምክንያት ስጋት ላይ ከወደቁትን አርሶ አደሮችን ጎን በመሰለፍ የደረሱ ሰብሎች በማጨድ፣ የታጨዱትን በመሰብሰብና ምርቱን ወደ ጎተራ በማስገባት ሲያገለግሉ ውለዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ውድድሮች መቋረጣቸውን ተከትሎ የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎች በጋራም ሆነ በተናጥል አስደሳች የሆኑ በጎ ተግባራት በመፈፀም የስፖርትን መርህ በተግባር ማሳየታቸው ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ወደፊትም እንዲህ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች መቀጠል እንዳለባቸው መልዕክታችን ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!