የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ቀሪ ስታዲየሞች ታወቁ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች ከአዲስ አበባ በመቀጠል የሚደረጉባቸው ስታዲየሞች ተለይተው ታውቀዋል፡፡

ሊጉ የፊታችን ቅዳሜ በሚወጣው ዕጣ ድልድል የመጀመሪያው ዙር ሙሉ መርሐ ግብር ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ውድድሩ በታኅሣሥ ወር ሲጀመር ኩባንያው የኮቪድ 19 ወረርሺኝን ለመቀነስ እንዲረዳው ውድድሮቹ የሚደረጉበትን ስታዲየም ቁጥር በመቀነስ ከጤና ጥበቃ ጋር በጋራ ስታዲየሞችን ከገመገመ በኃላ ለመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች የሚሆኑ ሦስት ሜዳዎችን አሳውቋል። አስቀድሞ የመጀመሪያ አርባ ጨዋታዎች (አምስት ሳምንታት) በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲደረጉ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ከአዲስ አበባ በመቀጠል የሚደረጉበትን ስታዲየሞች ለክለቦች አሳውቋል፡፡ በዚህም መሠረት የጅማ ስታዲየም እና የባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየሞች ቀሪ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ሜዳዎች መሆናቸውን የሊግ ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ምንም እንኳን የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ሜዳዎችን ኃላፊው ባይገልፁም ባገኘነው መረጃ መሠረት የድሬዳዋ፣ የሀዋሳ እኛ መቐለ ስታዲየሞች ለሁለተኛው ዙር መርሀ ግብር ማካሄጃነት ታስበዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!