“ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያክል ታሪካዊ ቡድን ከምርጥ ተጫዋቾች ጋር አብሮ መስራት ችሎታ ብቻ ሳይሆን ዕድለኝነትንም ይጠይቃል” ተስፈኛው ፉአድ ሀቢብ

አጭር ከሆነ የፕሮጀክት ቆይታ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ዘንድሮ በዝግጅት ላይ የሚገኘው እና ለወደፊት ጥሩ አማካይ እንደሚሆን የሚገመተው ፉአድ ሀቢብ የዛሬው የተስፈኞች አምዳችን ዕንግዳ ነው።

በቀደመው ዘመን በተለይ ከሰማንያዎቹ መጀመርያ አንስቶ እስከ ሚሌኒየሙ አጋማሽ ድረስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊዎችን ከታችኛው ቡድን በሂደት አብቅቶ በዋናው ቡድን በማጫወት አምበል ከመሆን ጀምሮ በርካታ ታሪክ የሰሩ ትውልዶችን ለራሱ ለክለቡም ሆነ ለሀገርም ሲያፈራ መቆየቱ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ሆኖም ያለፉትን ስድስት ዓመታት ከሚታወቅበት ባህል በማፈንገጥ በዘላቂነት ተከታታይነት ያለው የመሰለፍ ዕድል እያገኙ ከታዳጊ ቡድኖቹ ወደ ዋናው ቡድን አድገው የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በፈረሰኞቹ ቤት መመልከት አዳጋች ሆኗል። በየዓመቱ ጥሩ አቅም ኖሯቸው ተስፋም ተጥሎባቸው ስድስት ፣ ሰባት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን አድገው ልምምድ ቢሰሩም የመሰለፍ ዕድል በማጣት የውሀ ሽታ ሆነው ባክነው ሲቀሩም ይታያል።

ይህን ለማለት የወደድነው በዛሬ የተስፈኛ አምዳችን ዕንግዳ የሆነው ሶከር ኢትዮጵያ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በሜዳ ላይ አስገራሚ እንቅስቃሴው በቅርብ ርቀት ስትከታተለው በቆየችው ታዳጊ ተጫዋች ምክንያት ነው። በቁመቱ አጠር ቢልም መሀል ሜዳ ላይ የሚያስፈልገውን ነገር አሟልቶ የያዘው እና በአዕምሮው የሚጫወት ፣ የቡድን ሚዛንን ለመቆጣር ጉልበት ፣ ፍጥነት እና የፈጠራ ክህሎት ያለው ፣ ለአጥቂዎች አመቻችቶ ለጎል የሚሆኑ ኳሶች ከማቅረቡ ባሻገር ጎልም የሚያስቆጥረው ሁለገቡ አማካይ ፉአድ ሀቢብ ልናወራቹ ወደናል።

ሳሪስ የተወለደው ይህ ተስፈኛ በሰፈሩ በፕሮጀክት ታቅፎ ከሚሰራበት ቡድን በ2010 ወደ መከላከያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ቢያመራም በተለያዩ ሁኔታዎች ምክንያት ከመከላከያ በመውጣት በአሰልጣኝ ደረጄ ምርጫ በ2011 የቅዱስ ጊዮርጊስን ከ17 ዓመት በታች ቡድንን ተቀላቀለ። በ2011 የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት በአስር ቡድኖች መካከል በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር ላይ በሁሉም ጨዋታዎች በመሰለፍ ከላይ የገለፅነውን የሚያድግ ችሎታውን አሳይቷል። በ2012ም ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ20 ዓመት በታች ውድድር በኮሮና ቫይረስ እስከ ተሰረዘበት ጊዜ ድረስ በጥሩ ብቃት ፈረሰኞቹን አገልግሏል። ዘንድሮ ደግሞ ከዋናው ቡድን ጋር በመሆን ቢሸፍቱ ከገቡ ከታችኛው ቡድን ካደጉ ስድስት ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን ችሏል። ምንም እንኳን በዚህ ዕድሜው በፍጥነት ሰብሮ በመግባት በዋናው ቡድን ለመጫወት አስቸጋሪ ሊሆንበት ቢችልም ከዋናው ቡድን ጋር ዝግጅት መግባቱ ለነገ የእግርኳስ ህይወቱ ጥሩ መነሳሻ እንደሚሆነው ይገመታል። ይህን ሁሉ ያልንለት ተስፈኛው ወጣት ፉአድ ሀቢብ በዛሬው የተስፈኞች አምዳችን ዕንግዳ በመሆን ወደ ፊት ስለሚያስባቸው እና አሁን ስላለበት ሁኔታ በአጭሩ ነግሮናል።

“በተፈጥሮ ያገኘሁት ክህሎት ላይ አሰልጣኝ ደረጄ ብዙ ነገር ጨምሮልኛል ፤ ጥሩም ደረጃ ደርሻለሁ ፤ ብዙ የሚቀሩኝ ነገሮች ቢኖሩም። አሁን በቢሸፍቱ ከዋናው ቡድን ጋር ዝግጅት ገብቼ እየሰራው ነው። ይህ ለኔ በጣም ትልቅ ዕድል ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያክል ታሪካዊ እና ትልቅ ቡድን ውስጥ በሀገሪቱ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች ጋር አብሮ መስራት ችሎታ ብቻ ሳይሆን ዕድለኝነትንም ይጠይቃል። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። ራሴን አዘጋጅቼ አሰልጣኞቹ የሚሰጡኝን ልምምድ ተቀብዬ ነገ በትልቅ ደረጃ ለመጫወት እየሰራሁ ነው። ወደ ፊት ጥሩ ቦታ ደርሼ በጊዮርጊስ ቤት ማገልገል እፈልጋለው። ከዛም አልፎ ከኢትዮጵያ ውጪ ወጥቼ መጫወትን አስባለሁ። በመጨረሻ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ በመጀመርያ አሰልጣኝ ደረጄን አመሰግናለሁ። በመቀጠል እናቴ ለእግርኳስ የተለየ ቦታ አላት እና በብዙ መንገድ ስለረዳቺኝ እርሷንም አመሰግናለሁ። ሌላው የፕሮጀክት አሰልጣኜ አሰፋን ላመሰግን እወዳለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!