የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ሊሾም ነው

በዘጠናዎቹ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች መሐል የሚመደበው እንድርያስ ብርሀኑ ለኢትዮጵያ 17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በፌዴሬሽኑ ተመርጧል።

ከወራት በኃላ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ከታህሳስ 13-28 ጀምሮ የሚደረገውን ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች የሆነውን እንድርያስ ብርሀኑን የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም የወሰነ ሲሆን በዛሬው ዕለት ድርድር ካደረጉ በኃላ የቅጥር ስምምነቱ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ እንድርያስ በኢትዮጵያ መድን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መከላከያ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ እና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ረጅም ዓመት ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት የተለያዩ ቡድኖችን በዋናነት አልመዳ ጨርቃጨርቅ፣ ደደቢት በምክትል እና ዋና አሰልጣኝነት፣ ሰበታ ከተማን በምክትልነት፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎን በዋና አሰልጣኝነት ከሰራ በኃላ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ትኩረቱን ታዳጊ ላይ በማድረግ የኢትዮጵያ መድን ከ17 እና ከ 20 ዓመት በታች ቡድኖችን በመያዝ ስኬታማ ቆይታ አድርጓል። ዓምና የዋናው ቡድን ምክትል ሆኖም ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል። በታዳጊ ላይ ያመጣውን ስኬትና ልምድ ከግምት ያስገባው ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ ለመምረጥ እንዳበቃው ለማወቅ ችለናል።

በምድብ 2 ከዩጋንዳ እና ኬንያ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ ጥሩ ጉዞ በማድረግ አሸናፊ ወይም ሁለተኛ ሆና የምታጠናቅቅ ከሆነ የምስራቅ እና መካከለኛውን ቀጠና በመወከል በ2021 በሞሮኮ በሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ በቀጥታ የመሳተፍ እድል ይኖራታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!