” እኔ እንደ ተጫዋች የራሴን መስፈርት አውጥቼ ከቀረበልኝ ነገር ጋር አመዛዝኜ ንግድ ባንክን ተቀላቅያለሁ” – ሎዛ አበራ

አመሻሽ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች መሆኗ በይፋዊ የማብሰሪያ ሥነ-ስርዓት የተገለፀው ሎዛ አበራ ከፕሮግራሙ መገባደድ በኋላ ሀሳቧን አጋርታናለች።

ለተከታታይ ሦስት ጊዜያት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከደደቢት ጋር ያገኘችው ሎዛ አበራ በዛሬው ዕለት በይፋ የንግድ ባንክ ተጫዋች መሆኗ ተረጋግጧል። ተጫዋቿም በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራውን ስብስብ በመቀላቀል ለአንድ ዓመት 75 ሺ ወርሃዊ ክፍያ (50 ሺ ደሞዝ እንዲሁም 25 ሺ ፕሮፌሽናል ፕሌየር አሎዋንስ) በዓመቱ መጨረሻ ከሚሰጣት ጥቅማጥቅም ውጪ በማግኘት ፊርማዋን አኑራለች። ከፊርማ ሥነ-ስርዓቱ በኋላም ተጫዋቿ በተከታዮቹ ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሾችን ሰጥታናለች።

የዛሬው የማብሰሪያ ሥነ-ስርዓት በኢትዮጵያ የተጫዋቾች የዝውውር ታሪክ ያልተለመደ ነው። ምን ተሰማሽ?

እንደታየው ዛሬ የነበረው ፕሮግራም በጣም ቆንጆ ነበር። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረገውን ነገር ሌሎችም ክለቦች ማድረግ አለባቸው። ስለዚህ ክለቦች ይህንን ተሞክሮ ለሌላ ጊዜ ወስደውት ለተጫዋቾቻቸው ክብር ሰጥተው ቢያስፈርሟቸው በጣም ደስ ይለኛል።

ቀጣዩን የእግርኳስ ህይወትሽን ከአዲሱ ትዳር እና ክለብ ጋር እንዴት ታስኬጂዋለሽ?

ዓምና በቢርኪርካራ የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር። የዓምናው የስኬት ጊዜያትም ተገድበው አይቀሩም። ወደፊትም ይቀጥላሉ። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተነጋግረን አንድ ላይ ለመስራት ተስማምተናል። አዲስ በጀመርኩት ትዳርም በጣም ደስተኛ ነኝ። ትዳሬ ራሱን የቻለ ህይወቴ ነው። እግርኳስ ደግሞ ስራዬ ነው። ስለዚህ ሁለቱንም በጥሩ ሁኔታ ለማስኬድ አስቤያለሁ።

ከሀገር ውጪ በመጫወትሽ ምን አገኘሽ? ያለሽን ልምድ ለሌሎች የሀገር ውስጥ ተጫዋቾ እንዴት ለማጋራት ታስቢያለሽ?

እኔ ገና የተሻለ ደረጃ እንደምንደርስ ይሰማኛል። እኛ ብቻ ሳንሆን ከእኛም በኋላ የሚመጡ ተጫዋቾች የተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ አይቻለሁ። ሁሉም ሴት እግርኳስ ተጫዋቾች ከሀገር ውጪ ወተው መጫወት ይችላሉ። እኔም ባለኝ ልምድ እና ዕውቀት ተጫዋቾችን ለመርዳት እና ለማገዝ ዝግጁ ነኝ። በተወሰነ እና ባነሰ መልኩም ቢሆን መንገዱን የማቀው ያየሁትን ነገር ለተጫዋቾች አካፍላለሁ። ሲጀምር እግርኳስ ላይ ምንም የተለየ ነገር የለም። ሁሉም ራሱን ብቁ ካደረገ እና በደንብ ከሰራ የትኛውም ቦታ ወጥቶ መጫወት ይችላል። ዋናው ነገር ሙያን ማክበር፣ ለሙያ መገዛት እና በቅንነት መስራት ነው።

ከንግድ ባንክ በፊት ከየት የት ክለቦች ጥያቄዎች ቀረቡልሽ?

በነገራችን ላይ ከውጪ የመጡ ጥያቄዎች ነበሩ። ግን ኮቪድ-19 አብዛኛውን ክለብ በፋይናንስ ረገድ ስላሽመደመደ እና ለእኔ ከውጪ የመጣልኝን እድል ለማሳካት ኢምባሲዎች በበሽታው ምክንያት ክፍት ስላልነበሩ የውጪ እድሉ ሂደቱ ረዘመ። ሂደቱም የረዘመ እና የተንዛዛ ስለሆነ እድሎቹን ገታሁዋቸው። በሀገር ውስጥ ደግሞ መከላከያ ጥያቄ አቅርቦልኛል። ግን እኔ እንደ ተጫዋች የራሴን መስፈርት አውጥቼ ከቀረበልኝ ነገር ጋር አመዛዝኜ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተቀላቅያለው። ባንክ ያለው ስብስብም ጥሩ ስለሆነ ክለቡን መርጫለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!