ሎዛ አበራ ንግድ ባንክን በይፋ ተቀላቀለች

የሉሲዎቹ የፊት መስመር ተጫዋች ከአንድ ዓመት የአውሮፓ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሯ የተመለሰችበትን ዝውውር አከናወነች።

በዱራሜ ተወልዳ በክለብ ደረጃ ያላትን ህይወት ወደ ሀዋሳ ከተማ በመሄድ የጀመረችው ሎዛ አበራ በሀዋሳ ከተማ ራሷን ካሳየች በኋላ 2007 ላይ ወደ ደደቢት መጓዟ ይታወሳል። ተጫዋቿ በዚህ ክለብ በቆየችባቸው አራት ዓመታትም የሊጉን ዋንጫ ለ3 ተከታታይ ጊዜያት በማግኘት፣ 4 ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና 1 ጊዜ የሊጉ ኮከብ ተጫዋች በመሆን የእግርኳስ ህይወቷን በጥሩ መንገድ አስቀጠላለች። በዚህ ምርጥ ብቃቷም ከሃገሯ ወጥታ መጫወት የምትችልበትን አጋጠሚ አገኝታ ጉዞዋን ወደ ሲውድን አድርጋለች። በሲውድኑ ክለብ ከንግስባካ ለግማሽ ዓመት ግልጋሎት ከሰጠች በኋላ ዳግም ወደ ሃገሯ በመመለስ አዳማ ከተማን በግማሽ ዓመት ውል ተቀላቅላ የሊጉን ዋንጫ ለሦስተኛ ጊዜ ከፍ አድርጋለች። ዓምና ደግሞ ወደ ማልታው ክለብ ቢርኪርካራ በማምራት የቡድን እና የግል ስኬቶችን አግኝታ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች። በዛሬው ዕለትም በኢትዮጵያ የተጫዋቾች የዝውውር ታሪክ ባልተለመደ መልኩ በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በአንድ ዓመት ውል መቀላቀሏ ይፋ ሆኗል።

10:30 ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሠብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው የማብሰሪያ ሥነ-ስርዓት ላይ የባንኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓሊ አህመድ ጨምሮ የቦርድ አባላት ተገኝተዋል። ከክለቡ የበላይ ሃላፊዎች በተጨማሪም የእግርኳስ ቡድኑ አሠልጣኞች እና የቴክኒክ ሀላፊዎች በቦታው ተገኝተዋል። በቅድሚያም የባንኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓሊ የመክፈቻ ንግግር በአጭሩ ካደረጉ በኋላ ከሎዛ አበራ ጋር የስምምነት ፊርማ ሥነ-ስርዓት አከናውነዋል። 2008 ላይ 57 ጎሎችን ያስቆጠረችው ሎዛ በይፋ የክለቡ ተጫዋች መሆኗን በፊርማዋ አረጋግጣለች።

በአንድ ጨዋታ (እቴጌ ላይ) ዘጠኝ ጎሎችን በማስቆጠር በአንድ ጨዋታ ብዙ ጎሎችን ከመረብ ያገናኘች ብቸኛዋ የሀገራችን ተጫዋች የሆንው ይህቺ አጥቂ በአንድ ዓመት በክለቡ በሚኖራት ቆይታ በወር 50 ሺ ብር (ያልተጣራ) እንደምታገኝ ተገልጿል። በተጨማሪም ክለቡ በውስጥ ውል ባዘጋጀው የፕሮፌሽናል ፕሌየር አሎዋንስ ውል በወር ተጨማሪ 25 ሺ (ያልተጣራ) እንደምታገኝ ተነግሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጫዋቿ በዓመቱ መጨረሻ ኮከብ ተጫዋች ወይም ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆና ክለቧ የሊጉ አሸናፊ የሚሆን ከሆነ 100 ሺ ተጨማሪ ቦነስ እንደሚሰጣት በመግለጫው ተብራርቷል።

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሎዛ በተጨማሪ ከቀናት በፊት በፌዴሬሽን ያስፈረማትን ሰናይት ቦጋለን በይፋ ለጋዜጠኞች አስተዋውቋል። በኮካ ኮላ ውድድር ታይታ ቢኒ ትሬዲንግ ቡድንን የተቀላቀለችው ሰናይት ጥሩ ብቃቷን በማሳየት ወደ ደደቢት በማምራት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መጫወት መጀመሯ ይታወሳል። እስከ 2010 በቆየችበት ደደቢትም ሦስት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ አንስታለች። ከዛም ወደ አዳማ ከተማ በመጓዝ ተጨማሪ የሊጉን ዋንጫ 2011 ላይ ከፍ ማድረጓ ይታወሳል። 2010 ላይ የሊጉ ኮከብ ተብላ የተመረጠችው ይህቺ ተጫዋች ለሁለት ዓመት በባንክ ቤት ለመቆየት ፊርማዋን ከቀናት በፊት ብታሰፍርም ዛሬ በይፋ ክለቡን መቀላቀሏ በሥነ-ስርዓቱ ታይቷል።

ከሥነ-ስርዓቱ በኋላ ሎዛ አበራ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ከቆይተ በኋላ ይዘን እንቀርባለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!