የፕሪምየር ሊጉ ተጫዋቾች እና የኮሮና ቫይረስ  ጉዳይ…

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው የኮቪድ 19 ምርመራን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን በውጤቱም በቫይረሱ የተያዙ ተጫዋቾች እኛ አሰልጣኞች እየተገኙ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ታኅሣሥ 3 እንደሚጀመር የሊግ ካምፓኒው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አስራ ስድስት ክለቦችን የሚያወዳድረው የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ካለፉት ዓመታት ዘንድሮ በይበልጥ በተሻለ ቁመና ላይ ሆኖ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ በበላይነት እንዲሁም በዲኤስቲቪ ስፖንሰር አድራጊነት እንደሚደረግ የሚጠበቀው የ2013 ውድድር ከመጀመሩ በፊት ክለቦች የኮቪድ 19 ምርመራን ለተጫዋቾቻቸው እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ከስምንት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቡድን አባላት ውስጥ አስራ ስድስት ሰዎች ላይ የኮቪድ 19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡

ከሰበታ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ውጪ ያሉ የሊጉ ክለቦች ተጫዋቾቻቸው ወደ ልምምድ ከመግባታቸው በፊት የኮቪድ 19 ምርመራን በማድረግ ዝግጅታቸው የጀመሩ ሲሆን ከአስራ ሦስቱ ቀሪ የሊግ ክለቦች ስምንቱ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸው ወደ ማቆያ መግባታቸውን ሰምተናል፡፡ ምንም እንኳን ተጫዋቾቹም ሆኑ ክለቦቹ ስማቸውን ለድረ ገፃችን ከመግለፅ የተቆጠቡ ቢሆንም ቫይረሱ ከተገኘባቸው አስራ ስድስት ግለሰቦች መካከል ሦስቱ አሰልጣኞች መሆናቸው አረጋግጠናል፡፡

ይህም ቢሆን ክለቦች የኮቪድ 19 ምርመራን በማድረግ ወደ ዝግጅት የገቡ ሲሆን በካምፕ ራስን ጠብቆ ልምምድ መስራት ሲገባቸው ከካምፕ ወጥተው ከማኅበረሰቡ ጋር በድጋሚ መታየታቸው ሌላ ተጨማሪ ስጋትን በየክለቦቹ ይዞ መምጣቱ እንደማይቀር ባደረግነው ዳሰሳ መመልከት ችለናል። ይህ መሆኑ ደግሞ ውድድሩ ከጀመረ በኃላ ተጨማሪ ስጋት የሚያጭር ሆኖ ብቅ እንደሚል መገመት አያዳግትም፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!