ስለንስር አዳማ እግርኳስ አካዳሚ በጥቂቱ

በንስር እግርኳስ አካዳሚ ዙሪያ ከመስራቹ ጌታባለው ዘሪሁን ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበንላችኋል።

ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮች እና መፍትሄ በምናወራበት ወቅት በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ እንደመፍትሄ ሃሳብ የሚሰነዘረው ታዳጊዎች ላይ የመስራት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተለምዶው ከመነገሩ ባሻገር ይህ ነው የሚባል ፣ ወጥ የሆነ እና ትክክለኛ ለውጥን የሚያመጣ ሥራ አላስተዋልንም፡፡

በ2012 መስከረም 17 ነው የተመሰረተው ፤ ንስር አዳማ እግርኳስ አካዳሚ። ምንም እንኳን በትንሽ የሰው እና የገንዘብ አቅም ቢጀመርም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ እርምጃዎችን መራመድ ችሏል፡፡ መስራቹ ጌታባለው ተወልዶ ያደገው ቡልጋሪያ አካባቢ ሲሆን 38 በሚባለው ሜዳ እግርኳስን ሲጫወት እንዳደገ እና የነበረበት አካባቢ ስፖርቱን የሚወዱ ሰዎች የነበሩበት በመሆኑ ምክንያት ልዩ ፍቅር እንዳደረበት ይናገራል፡፡ ከኢትዮጵያ እግርኳስ የሚሰጡ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን በመውሰድ ሰርቲፊኬት ማግኘት የቻለ ሲሆን በትዳር ምክንያት ወደ አዳማ ከተማ ከሄደ በኋላ አካዳሚውን ለመጀመር ሀሳቡ መጥቶለታል፡፡ ከጌታባለው ጋር በአካዳሚው ዙሪያ ባደረግነው ቆይታ ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥቶናል።

“በመጀመሪያ ደረጃ ንስር አዳማ እግርኳስ አካዳሚን የእግርኳስ ችሎታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማራመድ የሚፈልጉ ታዳጊዎችን በመያዝ እና ከአልባሌ ነገሮች ርቀው እግርኳሱን በዕውቀት እንዲሰሩ ጤናቸውንም እንዲጠብቁ ለማድረግ ነው የሚሰራው፡፡ በተጨማሪም ትብብርን እና ስፖርታዊ ጨዋነትን በአፅንኦት ለማስቀጠል ይተጋል፡፡”

“ታዳጊዎች ወደ አካዳሚው ከመግባታቸው በፊት የቁመት እና ክብደት መጠናቸውን የሚያሳይ ወረቀት ከፋርማሲ ይዘው ይመጣሉ፡፡ የልደት ሰሪቲፊኬት የማቅረብ ግዴታም አለባቸው፡፡ ከዚያም የአንድ ዓመት ውል ይፈርማሉ፡፡ ይህ የሚሆነውም ከአንድ አካዳሚ ወደ ሌላ በመዘዋወር እንዳይባክኑ ነው፡፡”

“የመጀመሪያው ግቡ ታዳጊዎች ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለጎረቤቶቻቸው ፣ ለጓደኞቻቸው ብሎም ለሀገራቸው ፍቅር እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። በመቀጠልም ታዳጊዎቹ ከምንም ነገር በፊት በሥነ -ምግባር የታነፁ እና ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። በመጨረሻም በየትኛውም ቦታ ለሚጫወቱበት መለያ ፍቅር እና ተአማኒነት ኖሯቸው ራሳቸውን ፣ ክለቦቻቸውን ብሎም ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ባለመልካም ስብዕና ታዳጊዎችን ማፍራት ነው።”

“አሁን ባለው ሁኔታ ምንም ዓይነት ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም፡፡ እንደዚሁም ለጊዜው ውጪ ካሉ ክለቦች ወይም ግለሰቦች ጋር መሰረት የያዘ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም። ለመንግሥትም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት ማስተላለፍ የምንፈልገው መሬት ተወርዶ እንዲሰራ በባዶ ተስፋ ወይም ለሚዲያ ሽፋን ብቻ ሳይሆን ሁሉም በየኃላፊነቱ ታዳጊዎችን ማየት እና ማበረታት እንደሚያስፈልግ ነው። የግድ የተለየ ድጋፍ መሆን አይጠበቅበትም ፤ ታዳጊዎቹን ማበረታታቱ ራሱ ትልቅ ሞራል ነው። ከዚያ በተጨማሪም የተለያዩ የእግርኳስ ዕቃዎችን ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ለአሰልጣኞችም ሥልጠናዎችን ቢያመቻቹላቸው መልካም አቅጣጫዎችን ቢያሳዩዋቸው መልካም ነው። በተጨማሪም በጣም ልክ ያልሆነውን እና የመጥፎ መንገድ ጅማሬ እየሆነ የመጣው ከታዳጊዎች ጀምሮ እስከ ላይ አሰልጣኞች ድረስ እርስ በርስ መጠላላት መጠላለፍ ፣ ስም ማጥፋት እና የመሳሰሉትን እኩይ ተግባራት የተለያዩ መልካም ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በማወያየት ፣ አሰልጣኞችን በማቀራረብ ችግሮችን መፍታት ከዛም አለፍ ሲል በየክልሉ የታዳጊዎች ውድድር በማዘጋጀት ለሀገሪቷም ሆነ ለአህጉሪቱ የሚጠቅሙ ተጫዋቾችን ማፍራት ቢቻል መልካም ነው።”

“በግለሰብም ይሁን በመንግሥት ደረጃ ማንኛውም የእግርኳስ ዕቃዎችን ድጋፍ እንዲያደርጉልን እሱ እንኳን ባይሆን ካላቸው ጊዜ 10 ደቂቃም ቢሆን ወስደው ታዳጊዎቹን መጥተው ቢያበረታቷቸው ሞራል ቢሰጧቸው ቢመክሯቸው እጅግ የተሻለ ነው፡፡”

“በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ለማንኛውም የእግርኳስ ወዳድ የሆኑ የየትኛውም ሀገር ዜጎች ዩቲዩብ ገፃችንን ሰብስክራይብ እንዲያደርጉ ፣ ህሊናቸው እና አቅማቸው በፈቀደ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ፣ ሌላው እንኳን ባይሆን ዓለም ባመጣችልን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተለያዩ አፕሊኬሽኖች ታዳጊዎችን በቪዲዮ ኮል Live ቢመክሩ ቢያበረታቱ አሰልጣኙንም ሀሳቦችን ቢያጋሩት ቢያወያዩት ራሱንም የሚያሻሽልበት ዕድሎችን ቢያመቻቹ መልካም ነው።”

“ሌላው ደሞ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ክለቦች ነው። ታዳጊዎቹን መጥተው ቢያዩዋቸው ፣ ቢያበረታቷቸው እና ዕድል ቢሰጧቸው ምልመላዎች ሲኖሩም ቢያሳውቁን መልካም ነው።”

“በመጨረሻም በአመዴ የጤና ማዕከል የሚሰሩ የጤና ቡድኖች ለበረከቱልን መለያዎች እንዲሁም ነዋሪነቱ ስዊዘርላንድ ያደረገው ናትናኤል አሸናፊ ላደረገልን ድጋፍ እና ሰንዴይ ሙቱኩ ፣ ጃኮብ ፔንዜ ፣ ኢስማኤል ሳንጋሬ አካዳሚያችንን ጎብኝተው ተጫዋቾቻችንን ስላበረታቱ እና የበኩላቸውን ስካደረጉ እናመሰግናለን።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!