የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሴቶች አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን የውድድር መመሪያ ደንብን በዛሬው ዕለት ለክለቦች ሲያቀርብ የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብርም አከናውኗል።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚከወኑት የኢትዮጵያ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሊግ ውድድሮችን በተመለከተ ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ የደንብ ውይይት እና የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ሲከናወን ውሏል። ይጀመራል ተብሎ ከተነገረበት ጊዜ አንድ ሰዓት አርፍዶ በተጀመረው በዚህ መርሐ-ግብር ላይ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ አባላት፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን ወክለው አመራሮች ተገኝተዋል።
በቅድሚያም የሴቶች ልማት ውድድር ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጌታቸው የማነብርሃን (ኢንስፔክተር) ለ2013 የተዘጋጀውን የውድድር ደንብ በስፍራው ለተገኙ አካላት አስረድተዋል። 21 ገፆች ባሉት በዚህ የውድድር ደንብ ላይ ከቀደሙት ህጎች በተጨማሪ የ2021 የፊፋ አዲሱ የእግርኳስ ህግ እና አስገዳጅ የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ማስፈፀሚያ ህጎች መካተታቸው በዝርዝር ተብራርቷል። በተለይ ደግሞ በዋናነት ክለቦች ኮቪድን ታሳቢ እያደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ የሚያስር ህጎች በተለያዩ አንቀፆች መቀመጣቸውም ተነግሯል። ኢንስፔክተር ጌታቸው ዘለግ ላለ ደቂቃ የውድድሩን ደንብ ለተሳተፊ ክቦች ካብራሩ በኋላ የጨዋታ ፕሮግራምን በተመለከተ ኮሚቴው ለክለቦች ያቀረበውን አማራጭ ሃሳብ አንስተዋል። በዚህም ዋናው የሴቶቹ ውድድር ሀዋሳ እና አዳማ ላይ በሁለት ዙር ተደርጎ በአንድ ቀን ሦስት የጨዋታ መርሐ-ግብሮችን (4፣ 8 እና 10 ሰዓት) አልያም ሁለት የጨዋታ መርሐ-ግብሮች (4 እና 10 ሰዓት) እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ሁለተኛው አማራጭ በክለቦች ተመርጧል። በተመሳሳይ አንደኛውን ዙር ውድድር አዳማ አከናውነው ሁለተኛውን ዙሩ አዲስ አበባ የሚያደርጉት የሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊዎችም በተመሳሳይ በሁለተኛው አማራጭ ተስማምተዋል።
ደንቡን እና የውድድር ፕሮግራሙን በተመለከተ ገለፃ ከተደረገ በኋላ ከኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን ጋር በተገናኘ በሚመለከታቸው አካላት ሊተገበሩ የሚገባቸው ነገሮች ተብራርተዋል። በመቀጠልም በዳኞች ኮሚቴ እና በዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር አማካኝነት የውድድሩን ዳኞች የተመለከቱ የዝግጁነት ገለፃዎች በአቶ መኮንን እና አቶ ሚካኤሌ አማካኝነት ቀርቧል። በቋሚ ኮሚቴዎቹ አማካኝነት የተለያዩ ገለፃዎች ከተደረጉ በኋላ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሴቶች ልማት ውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ ቀደም ብሎ በቀረበው ደንብ ላይ ውይይት እንዲደረግ መድረኩን መምራት ጀምረዋል።
ረጅም ደቂቃ በፈጀው የውይይት መርሐ-ግብር ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ከክለብ አመራሮች የተሰነዘረ ሲሆን መድረኩም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሾችን በመስጠት ሥነ- ስርዓቱን አስቀጥሏል። በተለይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን በ2012 ደሞዝ ያልከፈሉ ክለቦችን ደሞዝ ለተጫዋቾቻቸው እንዲከፍሉ በአጽንኦት በመናገር ሃሳባቸውን ጀምረዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም እስካሁን በፌዴሬሽን ተገኝተው ምዝገባ ያላደረጉ ክለቦች በቶሎ እንዲመዘገቡ አደራ ብለዋል። ኃላፊው ቀጥለውም በአዲሱ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ያለውን ነገር ለተሳታፊዎቹ አጥርተዋል።
“የቻምፒየንስ ሊግ ውድድርን በተመለከተ አሁን ላይ የደረሰን ጥርት ያለ መረጃ የለም። ውድድሩ እንደሚካሄድ እናቃለን ግን መቼ እና የት እንደሚካሄድ ካፍ አላሳወቀንም። ግን ውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ክለቦች በቅድሚያ በየዞናቸው የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርገው ነው ስምንት ክለቦች በሚሳተፉበት የአህጉሪቱ ውድድር ላይ የሚካፈሉት። ስለዚህ እኛም አሁን ባለን መረጃ መሠረት በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በሴካፋ ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ያስፈልገናል። ግን እንዳልኳችሁ አሁን ላይ ካፍ የውድድሮቹን ቀናት አላሳወቀንም። ሴካፋም በአሁኑ ወቅት የእድሜ ቡድኖች ውድድርን ለማድረግ ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።” ብለዋል።
ከጽሕፈት ቤት ኃላፊው በመቀጠል የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሴቶች ልማት ውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ሶፊያ ክለቦች ለሴቶች እና ለወንዶች እኩል ዐይን እንዲኖራቸው ጠንካራ ቃላትን በመጠቀም ተናግረዋል። በተለይ ሰብሳቢዋ እንደ አቶ ባህሩ ሁሉ ክለቦች ደሞዝ በትክክል ለተጫዋቾቻቸው እንዲከፈሉ እና እንደ ወንዶቹ ሁሉ ተገቢ እንክብካቤ እንዲያደርጉ መማፀን በቀረው አማረኛ ተናግረዋል።
ከተሳተፊ ክለቦች የተነሱ ጥያቄዎችን መድረኩ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ የሁለቱ የሊግ እርከን ውድድሮች የዕጣ ማውጣት ፕሮግራም ተካሂዷል። በዚህም በቅድሚያ ዋናውን የአንደኛ ዲቪዚዮን (ፕሪምየር ሊግ) የጨዋታ መርሐ-ግብሮች ክለቦች ራሳቸው አውጥተዋል። በሁለት ዙር ሀዋሳ እና አዳማ ላይ በሚደረገው ውድድርም 11 ክለቦች እንደሚሳተፊ የተነገረ ሲሆን በመጀመሪያ ሳምንትም ተከታዩ መርሐ-ግብር ወጥቷል።
በሁለተኛው ዲቪዚዮን ውድድር ላይም አዲሱን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ በተመሳሳይ 11 ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር ውድድሩ አዳማ ሁለተኛው ዙር ደግሞ አዲስ አበባ ላይ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል። በወጣው መርሐ-ግብር መሠረትም በመጀመሪያ ሳምንት የሚገናኙት ክለቦች የሚከተሉት ወጥቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!