ዋልያዎቹ አሁንም በአቋም መፈተሻ ጨዋታ ድል ማድረግ አልቻሉም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታቸውን ከሱዳን ጋር በዛሬው ዕለት አከናውኖ 2-2 በሆነ ውጤት ጨዋታውን አገባዷል።

በቀጣይ ቀናት ከኒጀር አቻቸው ጋር ለካሜሩኑ የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ለማድረግ ዝግጅት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ዛሬ ሦስተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታቸውን ከሱዳን ጋር አከናውነው ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታውን ጨርሰዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በዛሬው ጨዋታ በ4-3-3 አስተላለፍ ተክለማርያም ሻንቆ፣ ሽመክት ጉግሳ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባዬ፣ ረመዳን ናስር፣ አማኑኤል ዩሃንስ፣ መሱዕድ መሐመድ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አቡበከር ናስር፣ ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በመጀመርያ አስራ አንድ ተጠቅሞ ጨዋታውን ቀርበዋል።

በጀብደኝነት ጨዋታውን የጀመሩት ዋልያዎቹ ገና በጊዜ መሪ የሆኑበትን ኳስ ከመረብ አገናኝተዋል። በሦስተኛው ደቂቃም የሱዳን ተከላካዮች ኳስ ወደ መሐል ለመላክ ሲሉ አቡበከር ተደርቦ የመለሰውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ጌታነህ ከበደ አግኝቶት ከሳጥን ውጪ በመምታት ግብ አስቆጥሯል። መሪ ከሆኑ በኋላም በኳስ ቁጥጥሩ የጨዋታውን የሃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ያደረጉት ባለሜዳዎቹ ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ በማብዛት ግጥሚያውን ቀጥለዋል። በተቃራኒው ከኳስ ጀርባ በመሰብሰብ ጨዋታውን የጀመሩት ሱዳኖች በበኩላቸው የሚያገኙትን ኳስ በመቀባበል ከግብ ክልላቸው ለመውጣት ቢሞክሩም ሀሳባቸው ብዙም ሳይሰምር ሲቀር ታይቷል።

በጊዜ መሪነቱን ያገኙት የአሠልጣኝ ውበቱ ተጫዋቾች በ17ኛው ደቂቃም የሱዳን ተጫዋቾች በድጋሜ ከግብ ክልላቸው ሳይርቁ የተቀባበሉትን ኳስ አቡበከር በጥሩ ቅልጥፍና አቋርጦ ለጌታነህ ሰጥቶት ጌታነህ በቀጥታ ኳሱን ወደ ጎል መቶት ግብ ጠባቂው ዓሊ አብደላ እድሉን አምክኖታበል።

ሱዳኖች በበኩላቸው በመጀመሪያ ደቂቃ ግብ ተቆጥሮበቸው እየተመሩ ቢሆንም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ምንም ጥረት ለማድረግ ፍላጎት ሳያሳዩ ጨዋታው ቀጥሏል። አልፎ አልፎ ግን ረጃጅም ኳሶችን በመላክ አጥቂያቸውን ለማግኘት ቢጥሩም ውጥናቸው የሰላ ሳይሆን ቀርቷል። በተቃራኒው ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ እያስኬዱ የነበሩት ባለሜዳዎቹ በ39ኛው ደቂቃ ሽመልስ በግራ መስመር እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ ለአማኑኤል በተረከዝ ያቀበለውን እና አማኑኤል ለጌታነህ ያሻገረውን የመሬት ለመሬት ኳስ የቡድኑ አምበል ሳይጠቀምበት የቀረበት ዕድም ለግብነት የቀረበ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በዋሊያዎቹ በኩል የተደረጉትን ሦስት ሙከራዎች የሰነዘረው ጌታነህ ከበደ ከኳስ ውጪ ወደ መሐል እየተሳበ ቡደኑን በመከላከሉ እና ኳስ በማስጣሉ ረገድ ሲያግዝ ተስተውሏል።

አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩትም ሱዳኖች በጥሩ አካሄድ የዋሊያዎቹ የግብ ክልል ደርሰው ነበር። ግን አጋጣሚውን ሳይጠቀሙት ቀርቷል። አጋማሹም በዋሊያዎቹ 1-0 መሪነት ተጠናቆ ተጫዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ አሠልጣኝ ውበቱ አማኑኤል ዩሃንስ እና አቡበከር ናስርን አስወጥተው ይሁን እንዳሻውን እና ጋዲሳ መብራቴን ወደ ሜዳ በማስገባት አጋማሹን ጀምረዋል። በተቃራኒው ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ አጋማሹን የጀመሩት ሱዳኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ ታይቷል። በ52ኛው ደቂቃም በመሐመድ አብዱራህማን አማካኝነት አቻ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። በዚህ ደቂቃ መሐመድ አብዱራህማን ከመሐል የተሠነጠቀለትን ኳስ የግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆን አቋቋም በመመልከት ከርቀት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ነበር ቡድኑን አቻ ያደረገው።

አጋማሹ በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ ግብ ያስናገዱት ዋሊያዎቹ በ54ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ በመታው ኳስ ዳግም መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ይህ ሙከራ በተደረገ በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የተላከውን ኳስ አቲር ኤል ጣሂር ራሱን ነፃ አድርጎ በመቆሙ ያገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ይህኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባነሰ ፍላጎት እና ፍጥነት ጀምረው ሁለት ጎሎችን ያስተናገዱት ዋሊያዎች በ65ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ታፈሰ ሰለሞን የቅጣት ምት አቻ ለመሆን ሞክረዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ72ኛው ደቂቃ ሱሌማን ሀሚድ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥን አሻግሮት ሳጥን ውስጥ የነበሩት ጌታነህ፣ ጋዲሳ እና ከነዓን አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት መክኗል።

በአንፃራዊነት ጨዋታውን መቆጣጠር የጀመሩት ዋሊያዎቹ ከመጀመሪያዎቹ የሁለተኛ አጋማሽ ደቂቃዎች በተሻለ ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ የጨዋታውን ደቂቃ ማሳለፍ ይዘዋል። በተቃራኒው የሚፈልጉትን ገና በአጋማሹ ጅማሬ ያሳኩት ሱዳኖች ግጥግጥ ብሎ በመከላከል የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመልሶ ማጥቃት ብቻ ለማግኘት ታትረዋል። የሱዳኖች ኳሱን አለመፈለግ የጠቀማቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በ88ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን በጥሩ ዕይታ ለአማኑኤል በአየር ላይ የላከለትን ኳስ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ አማኑኤል በግምባሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን አቻ ሆነዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት 2-2 በሆነ ውጤት ተገባዷል።

ይህንን የወዳጅነት ጨዋታ ለማከናወን ትናንት ቀጥር አዲስ አበባ የገቡት ሱዳኖች ነገ ረፋድ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በቀጣይ ወደሚያደርጉበት ጋና እንደሚያቀኑ ተሰምቷል። ዋልያዎቹ በበኩላቸው ነገ እና ከነገ በስትያ አዲስ አበባ በመቆየት ሰኞ ወደ ኒጀር ኒያሜ እንደሚጓዙ ተሰምቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!