በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ኢትዮጵያን በመወከል እየተጫወተ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲሸልሱ ሴንት ሚሸል ዩናይትድ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ወደ ስፍራው ሃሙስ ያቀናል፡፡
ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ በአዳነ ግርማ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ጎድዊን ቺካ ሶስት ግቦች አማካኝነት 3-0 ያሸነፉ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ በመጪው ቅዳሜ በዩኒቲ ስታዲየም ያደርጋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሲሸልስ የሚያቀናው 26 ልዑካንን ይዞ ሲሆን 4፡00 ሰዓት ላይ ጉዞ እንደሚጀምር ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡ 117 የሚጠጉ የክለቡ ደጋፊዎችም ክለባቸውን ለማበረታታት ወደ ስፋራው ይጓዛሉ፡፡ በ2002 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሱዳኑ ኤል ሜሪክ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ከሜዳው ውጪ ባደረገው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች ወደ ኦምዱሩማን አቅንተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የመልሱን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ በመጀመሪያው ዙር ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ይገናኛል፡፡ የማለፍ ሰፊ ዕድል ያለው ጊዮርጊስን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሴንት ሚሸል አሰልጣኝ አንድሪው ጅያን ሊዊ ከሁለት በፊት ሳምንት አዲስ አበባ ላይ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ያጋሩ