ካፍ ለሴቶች እግርኳስ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል

በካፍ እየተሰጠ የሚገኘው እና ኢትዮጵያዊያን የሴቶች እግርኳስ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ያለው ስልጠና ትናንት ተጀመረ፡፡

የአፍሪካ እግርኳስ ማኅበር (ካፍ) በስሩ ላሉ አባል ሀገራት ውስጥ ለሚገኙ የሴት እግር ኳስ አሰልጣኞች ባለሙያዎች እና በፊዚዮቴራፒስነት በሴት እግር ኳስ ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ለሦስት ቀን የሚቆይ የኦንላይን ስልጠና ጀምሯል፡፡ትናንት ረፋድ በጀመረው ስልጠና ላይ ከዚህ ቀደም በአካል ባለሙያዎቹ በአንድ ሀገር በሚሰጥ ስልጠናን ሲወስዱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ተሳታፊዎቹ በያሉበት እንዲወስዱ አዲስ መመሪያን በማስተላለፍ በኦንላይን ሊሰጥ ችሏል፡፡

ስልጠናው በዋናነት በካፍ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ሲሆን በእግር ኳስ ዕድገት እና ልማት ላይ ያተኮረ ነውም ተብሏል። የሴት ባለሙያዎች ተሳትፎ ላቅ እንዲል የተዘጋጀው ይህ ስልጠና በተጨማሪም በሴት እግርኳስ ላይ የሚሰሩ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎች ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ክንውኖችም ትምህርት ተሰጥቶበታል።

የፊታችን ረቡዕ ከሰዓት በሚጠናቀቀው በዚህ ስልጠና ላይ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን ጨምሮ ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዓይ፣ መሠረት ማኔ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው፣ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ከ17 አመት ብሔራዊ ቡድንን በመወከል ሳሙኤል አበራ በስልጠናው የተካፈሉ ሲሆኑ የመቐለ 70 እንደርታዋ አሰልጣኝ ህይወት አረፋይኔ በስልጠናው ተካፋይ የነበረች ቢሆንም በኔትወርክ ችግር ምክንያት ሳትሳታፍ ቀርታለች፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ በስልጠናው ተካፋይ የነበሩ አሰልጣኞችን ያነጋገረች ሲሆን ካፍ ለሴት እግር ኳስ ትኩረት አድርጎ ተጨንቆ ልክ እንደ ወንዶቹ ለመስራት መጋጀቱ እና ስልጠና መስጠቱ የሚያበረታታ ቢሆንም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሴቶች እግርኳስ ዝቅተኛ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ከስልጠናው ተሞክሮን ወስዶ ሊያርማቸው እና ሊሰራበት ይገባልም በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!