ሶከር ሜዲካል| የአዕምሮ መዛል በእግርኳስ [ክፍል 1]

በዚህ ሳምንት አምዳችን በእግር ኳስ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱ ስለሆነው ነገር ግን የሚገባውን ትኩረት ስላላገኘው የአዕምሮ መዛል (mental burnout ) እንመለከታለን።

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የእግር ኳስ ውድድሮች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የሀገራችን የክለቦች ውድድር ለመመለስ የተቃረበ ሲሆን ብሄራዊ ቡድናችንም በ3 የወዳጅነት ጨዋታዎች ወደ እግር ኳሱ ተመልሷል። በቅርብ ቀናትም ኒጀርን የሚገጥም ይሆናል።

እግር ኳስ ለረጅም ጊዜያት በተቋረጠበት ወቅት ድባቴ እና የመሳሰሉ የአዕምሮ ጤና ቀውሶች ተጨዋቾችንም ሆነ እግር ኳስን በፍቅር የሚከታተለውን ደጋፊ እንደሚያጠቃ አውርተን ነበር። አሁን ደግሞ በውድድሮች መደራረብ ከዛ ጋርም ተያይዞ ደግሞ በሚፈጠር ጫና ምክንያት የአዕምሮ መዛል አልያም መድከም ይፈጠራል የሚል ስጋት አለ።

በተለይም ከግንቦት ጀምሮ ያለበቂ እረፍት እየተደረገ በሚገኘው የአውሮፓ የሊግ ውድድሮች ብዙ ተጫዋቾች ለዚህ ችግር እንደሚጋለጡ ይጠበቃል። በቀጣዮቹ ወራት ጨዋታዎች በፍጥነት የሚመጡ ሲሆን ከአካላዊ ጉዳት በተጨማሪ የአዕምሮ ጫናውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ለዚህ ፅሁፍ ይረዳን ዘንድም The Athletic የተሰኘው የስፖርት ድረ ገፅ ስለ ጉዳዩ ያሰፈረውን ፅሁፍ እንደግብአት ተጠቅመናል። በአምዱ ላይ ስነ ልቦናዊ ጫናዎች በሶስት ዋና ዋና ረድፎች እንደሚከፈሉ ያትታል ።

ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነውን መዋቅራዊ ጫና በዚህ ፅሁፍ እንመለከታለን። እነዚህ በተጫዋቹ አቅራቢያ ያሉትን ከባባዊ ሁኔታዎች ይመለከታል። ከእነዚህ ምካከል ምሳሌ የሚሆኑት የአሰልጣኞች መቀያየር ፤ ከቡድን አጋሮችም ሆነ ከበላይ አካላት ጋር የሚኖር ግጭት እና በአጠቃላይ ከክለቡ በኩል የማይኖር ድጋፍን ይመለከታል።

በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ምንም አይነት ጫና ወይንም ችግር መቋቋም እንደሚችሉ ይታሰባል። ብዙ ገንዘብ ስለሚያገኙ እና ልምድ ስላላቸው ሁሉም ነገር ለእነርሱ ቀላል እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። እውነታው ግን ከዚህ እጅጉን የራቀ ነው።

ከ5 ዐመታት በፊት FIFA Pro ያደረገው ሰፊ ጥናት እንደሚያሳየው 38% የሚሆኑ ነባር ተጫዋቾች ድባቴ (depression) አልያም የጭንቀት ህመም (Anxiety) አለባቸው። እነዚህ የህመም ስሜቶች በበለጠ በሚመጡት ወራቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምሩ ይጠበቃል።

የስፖርት ስነልቦና ባለሙያ የሆነው ዴቪድ አብራሃምስ ተጫዋቾች ከሌላው ማህበረሰብ አንፃር ለአዕምሮ ህመም የሚኖራቸው ተጋላጭነት አናሳ ነው ብሎ ማሰብ ፈፅሞ የተሳሳተ እንደሆነ ይገልፃል።

” አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሱት ባላቸው ላቅ ያለ የእግር ኳስ ክህሎት የተነሳ እንደሆነ የታወቀ ነው። ነገር ግን የእግር ኳስን ስነልቦናዊ ዘርፍ በጥሩ ሁኔታ ይረዳሉ እና ያውቃሉ ብሎ ማሰብ የተሳሳተ አመለካከት ነው። እርግጥ ነው የተጫዋቾች ነገሮችን የመረዳት እና የመወጣት ብቃት የተለየ ነው። ነገር ግን ማወቅ ያለብን ጉዳይ በቂ ዕርዳታ ካገኙ ሜዳ ላይ ያለውንም ጫና ሆነ ከሜዳ ውጪ ያሉ ማህበራዊ እና አዕምሮአዊ ተግዳሮቶችን መቋቋም ይችላሉ።”

ያለ አዕምሮ ጤና ፤ ጤና የለም!

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!