ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲስ አሰልጣኝ ሲመርጥ በቀድሞ አሰልጣኙ ቅሬታ ቀርቦበታል

በቅርቡ የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ክፍሌ ቦልተናን አሰልጣኝ አድርጎ ሲመረጥ ከተወዳደሩ አሰልጣኞች መካከል ጉልላት ፍርዴ የቅሬታ ደብዳቤን አስገብተዋል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ እየተወዳደረ የሚገኘው ክለቡ ለ2013 የውድድር ዓመት አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከሳምንታት በፊት የቅጥር ማስታወቂያን ያወጣ ሲሆን ካወዳደራቸው በርካታ አሰልጣኞች ሰባቱን ለመጨረሻ የቃል ፈተና ዛሬ ረፋድ ጠርቶ ከፈተናቸው በኃላ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ቀጣዩ አሰልጣኝ መሆናቸውን ክለቡ ለአሰልጣኙ ገልጿል፡፡ ሆኖም ይህን ውጤት የሰሙት የቀድሞው የክለቡ አሰልጣኝ እንዲሁም የክለቡ ቴክኒክ ዳሬክተር በመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰሩ የነበሩት ጉልላት ፍርዴ “መወዳደር ሲገባኝ እንዴት አትወዳደርም ልባል እችላለሁ። ብዙ ውጤት ያስመዘገብኩ አሰልጣኝ ሆኜ እያለሁ ሲቪዬን አስገብቼ እጠራለሁ ብዬ ስጠብቅ አልተጠራሁም። ይሄ አግባብ አይደለም።” በሚል የቅሬታ ደብዳቤን ማስገባታቸው ታውቋል። 

ይህን ተከትሎም “በነገው ዕለት በድጋሚ የአሰልጣኝ ቅጥሩን ሁኔታ እና የጉልላት ፍርዴን አቤቱታ ለመመልከት በማሰብ የአሰልጣኝ ክፍሌን የሹመት ውሳኔ በድጋሚ ለመመልከት ተገደናል። ” ሲሉ ሥራ አስኪያጁ አቶ ለማ ደበሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!