የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከአህመድ ረሺድ ጋር…

በቅፅል ስሙ ሽሪላ እየተባለ የሚጠራው የዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ እንግዳችን አህመድ በመዲናችን አዲስ አበባ በተለምዶ አሜሪካ ግቢ እየተባለ በሚጠራው ሠፈር ነው ተወልዶ ያደገው። ከእግርኳስ ውጪ እምብዛም መዝናኛ በሌለበት ሀገራችንም ኳስን ብቸኛ ምርጫ በማድረግ እድገቱን አድርጓል። በተለይ ተጫዋቹ የሠፈሩ ልጅ የነበረውን አብዱረህማን ሙባረክን (አቡሸት) በመመልከት ለእግርኳስ ልዩ ፍቅር እንዳደረበት ይናገራል። በሰፈሩ በሚገኝ የመጫወቻ ሜዳ ውሎውን በማድረግም ለተሻለ ሥልጠና አውቶቢስ ተራ አካባቢ መቀመጫውን ወዳደረገው ጫካ ሜዳ የፕሮጀክት ቡድን ጉዞውን በማድረግ ቡድኑን ተቀላቀለ። በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ታዳጊዎችን የያዘው ይህ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥም ከ15 ዓመት በታች ስብስብን ተቀላቀለ። ተጫዋቹ አሠልጣኝ ታዲዮስ በሚያሰራበት በዚህ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ለሦስት ዓመታት እድገትን እያገኘ ቆይታን ካደረገ በኋላም በጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ላይ የሚሳተፍበትን እድል አገኘ። በውድድሩም ጥሩ ብቃትን በማሳየት በአሠልጣኝ ኤፍሬም ደምሴ (ቤቢ) አማካኝነት 2004 ላይ የደደቢትን ሦስተኛ ቡድን (C) ተቀላቀለ። በዚህ ቡድን የተዘጋጀው ውድድርንም በሻምፒዮናነት በማጠናቀቅ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ ሁለተኛው ስብስብ (B) አደገ። 2005 ላይ ክለቡ ደደቢት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ሲያገኘም ከሁለተኛ ቡድኑ ወደ ዋና ቡድኑ እየመጣ አልፎ አልፎ ግልጋሎት ይሰጥ ነበር።

ወደ ደደቢት ይዞት የገባው አሠልጣኝ ኤፍሬም (ቤቢ) 2006 ላይ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሲያቀናም አህመድ እና አምስት ተጫዋቾችን ከአሠልጣኛቸው ጋር አብረው ቡናማዎቹ ቤት ደረሱ። በቡና ተስፋ ቡድንም ጥሩ እድገትን በማሳየት በስብስቡ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላው በዋና ቡድኑ አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ተመርጦ ግልጋሎትን ይሠጥ ጀመረ። ከዛም በኋላም 2007 ላይ በአሠልጣኝ ጥላሁን እና አኑዋር አማካኝነት በቋሚነት የቡናማዎቹን መለያ ለብሶ በዋና ቡድን ውስጥ መጫወት ያዘ። እስከ 2009 ድረስም በወጥነት ለክለቡ የአቅሙን ከሰጠ በኋላ 2010 ላይ ወደ ምስራቂቱ የሃገራችን ክፍል ድሬዳዋ በማቅናት ለአንድ ዓመት ተጫወተ። ተጫዋቹ ለአንድ ዓመት በድሬዳዋ ከተጫወተ በኋላም 2011 ላይ ዳግም ጥሩ የስኬት ዓመታትን ወዳሳለፈበት ኢትዮጵያ ቡና በመመለስ መጫወት ቀጠለ። ዓምና ሊጉ በኮቪድ-19 ምክንያት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም ቡናማውን መለያ ለብሶ ከተጫወተ በኋላ ዘንድሮ የፋሲል ተካልኙ ባህር ዳር ከተማ ለማገልገል ፊርማውን አኑሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከቡድኑ ጋር እያደረገ ይገኛል።

በአሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን በኦሎምፒክ ደረጃ እንዲወክል ጥሪ የቀረበለት ተጫዋቹ ከዛም በኋላ በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አማካኝነት ዋናውን ቡድን እንዲወከወል ተመርጦ ለሀገሩ የአቅሙን ቸሯል።

አሁን ከሚገኝበት ባህር ዳር ከተማ በፊት ለሦስት የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የተጫወተው እና በሁለቱም እግሮቹ ኳስን በእኩል ደረጃ የሚጫወተው አህመድ ረሺድ ዛሬ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል። እኛም አጫጭር ጥያቄዎች አቅርበንለት ተከታዮቹን ምላሽ ሰጥቶናል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

እኔ እንደ አርዐዓያ ስመለከተው የነበረው አብዱረህማን ሙባረክን (አቡሸት) ነው። ምክንያቱም እርሱ ኳስን እንድወድ በጣም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከልጅነቴም ጀምሮ እሱን እያየሁ ነበር ያደኩት። በዚህ አጋጣሚ እንደውም እርሱን ላመሰግነው እፈልጋለው።

አሁን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ከመጀመራችሁ በፊት ሊጉ ለ7 ወራት ተቋርጦ ነበር። በእነዛ ዘለግ ላሉ ጊዜያት ጊዜህን በምን ነበር ስታሳልፍ የነበረው?

ለ7 ወራት ያለ ውድድር ከሜዳ መራቅ ለእኛ ስፖርተኞች በጣም ከባድ ነው። እኔ በግሌ ጊዜው ሲኦል ነበር የሆነብኝ። ምክንያቱም ከእግርኳስ ውጪ ሌላ ህይወት ስለማላቅ። በአጠቃላይ ግን የመጀመሪያዎቹን ወራት በጣም ተጨናንቄ ነበር ያሳለፍኩት። ከዛ ግን ፊቴን ወደ እምነቴ በማዞር የተለያዩ ትምህርቶችን ስማር ነበር። በተለይ የቁርአን ትምህርቶችን ስማር ነበር። ከዚህ ውጪ አቋሜን ለመጠበቅ የሚረዳኝን እንቅስቃሴዎች ስከውን ነበር።

ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ የለመድከው ልማድ አለ? በፊት የማታዘወትረው አሁን ግን ቤት በመቆየትህ የለመድከው ነገር?

እንደምታቀው እኛ ስፖርተኞች አብዛኛውን ጊዜያችንን ውድድር እና ልምምድ ላይ ነው የምናሳልፈው። ከዚህ የተነሳም ከማኅበራዊ ህይወት ትንሽ ራቅ ብለን ነበር። በሽታው ከመጣ በኋላ ግን ጊዜ ስላገኘሁ ይህንን ህይወቴን ለማስተካከል ጥሬያለሁ። ስለዚህ ማኅበራዊ ህይወቴን የማጠናከር ልማድ በዚህ ቆያታ ተምሬያለሁ።

በእግርኳስ ህይወትህ በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?

2008 ላይ ፖፓዲች ቡናን በያዘበት ዓመት የነበረኝ ነገር በጣም ምርጥ ነበር። እርግጥ ቡድናችን በመጀመሪያ ዙር ውድድር ጥሩ አልነበረም። ከዛ ግን በሁለተኛ ዙር ውድድር በጣም ተሻሽለን ነበር የቀረብነው። እንደውም እስከ ተበጠበጠበት የሀዋሳ ጨዋታ ድረስ ያለመሸነፍ ግስጋሴ ላይ ነበርን። ብቻ በጠቅላላው እኔም በግሌ ቡድኑም እንደ ቡድን ድንቅ የነበርንበት ጊዜ ነበር።

ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህ ምንድን ናቸው?

የምወደው ጠንካራ ጎኔ እልኽኘነቴን ነው። መሸነፍ አልወድም። በጭራሽ ክለቤ ተሸንፎ ከሜዳ እንዲወጣ አልፈልግም። ይህ ብቻ ሳይሆን የቡድን አጋሮቼ ሜዳ ላይ እንዲነኩ አልፈልግም። ከዚህ ውጪ እንደ ሰው ደካማ ጎንም ይኖረኛል። ግን እነዛን ደካማ ጎኖች ለማሻሻል እጥራለሁ።

አህመድ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

ያው ተወልጄ ያደኩት አሜሪካን ግቢ ነው። ያ አካባቢ ደግሞ የንግድ መሐከል ነው። ከዚህ መነሻነት ስንወጣ ስንገባ በመርካቶ ስለሆነ የምናልፈው እኔም የንግዱን ዓለም የምቀላቀል ይመስለኛል። እንደውም ንግዱን ትቼ እግርኳስ ተጫዋች በመሆኔ እድለኛ ነኝ።

ሜዳ ላይ የግራ እና የቀኝ እንዲሁም የመሐል ተከላካይ ሆነህ ስትጫወት እንመለከትካለን። አንተ በየትኛው ቦታ ነው መጫወት የምትመርጠው?

ማንኛውም አሠልጣኝ የትኛውም ቦታ አሰልፎ ቢያጫውተኝ እኔ አይከፋኝም። ለምሳሌ በፕሮጀክት ደረጃ ስጫወት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ነበርኩ። ከዛም አማካኝም ሆኜ ተጫውቻለው። አሁንም እንዳልከው ተከላካይ ሆኜ እየተጫወትኩ ነው። ስለዚህ የትኛውም ቦታ ለእኔ አዲስ ቦታ አደለም። አሠልጣኞች አምነውብኝ ያሰልፉኝ እንጂ እኔ ምንም ችግር የለብኝም። ግን አበላልጥ ካልከኝ የመሐል ተከላካይ ሆኜ ብጫወት ክለቤንም ሆነ ሀገሬን በደንብ ማገልገል እችላለሁ።

እዚሁ ላይ ግን በቀኝ እግርህም ሆነ በግራ እግርህ በእኩል ደረጃ በጥሩ ብቃት ትጫወታለህ። ይህንን ችሎታ እንዴት አዳበርከው?

እግርኳስ ተጫዋች በቻለው አቅም በሁለት እግሩ መጫወት ቢችል ጥሩ ነው። በሁለት እግር መጫወት የሚችል ተጫዋች ክለቡን ወይም ሀገሩን ከሚጠቅመው በላይ ራሱን ነው የሚጠቅመው። ምክንያቱም በየትኛውም ቦታ ተፈላጊ የመሆንን ጥቅም ስለሚሰጠው። እኔ አሁን በሁለት እግሬ መጫወት ባልችል ኖሮ እርግጠኛ ነኝ በቡና ቤት በቋሚነት ላልጫወት እችል ነበር። የመጀመሪያ ጨዋታዬንም ጎንደር ላይ ለቡና ስጫወት በዚህ አማካኝነት ነው ዕድል ያገኘሁት። ስለዚህ ራሴን እንደሚጠቅም ስለማቅ ነው ይህንን ችሎታ ያዳበርኩት።

በተቃራኒ ስትገጥመው የፈተነህ ወይም የከበደህ ተጫዋች አለ?

እውነት ለመናገር ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች በሀገራችን ይገኛሉ። ከሁሉም በላይ ግን ሳልሀዲን ሰዒድ ሜዳ ላይ ይከብደኛል። ልምድ ያለው፣ ዕይታው የሚገርም፣ ውሳኔዎቹ ብዙ ጊዜ ልክ የሆኑ እና የበሰለ አጥቂ ነው። ስለዚህ ሳላ ከባድ ነው። ከእርሱ በተጨማሪ አቡበከር ናስር ይፈትነኛል። አብረከው ስለተጫወትክ ነው እንዳልባል እንጂ አቡኪ በጣም ምርጥ ተጫዋች ነው። ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ለተከላካይ በጣም ፈታኝ ነው። ከዚህ መነሻነት እርሱም ይፈትነኛል።

እስቲ ምርጫ ላይ እንምጣ። አሁን ላይ ከሚገኙ የሀገራችን ተጫዋቾች የአንተን ምርጥ ንገረኝ?

እኔ በአንደኛነት የምመርጠው ተጫዋች አቡበከርን ነው። አቡኪ ምርጥ ላይ ነው ያለው። እንደውም ኢትየጵያ ውስጥ መጫወት የለሌበት ጎበዝ ልጅ ነው። በአውሮፓ ደረጃ መጫወት የሚያስችል ትልቅ አቅም ያለው በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው።

ይህንኑ ጥያቄ ወደ አሠልጣኞች እንውሰደው። ከአሠልጣኞችስ?

ምንም ጥያቄ የለውም አሁን ባህር ዳር ከመግባቴ በፊት ቡና ቤት እያሰራኝ የነበረው ካሳዬ አራጌ ምርጡ አሠልጣኝ ነው። ካሳዬ ለቡና ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ትልቅ ነገር ነው እየሠራ ያለው። ዓምና ስድስት እና ሰባት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሰራውን ነገር አይተናል። ስለዚህ ወደፊት ደግሞ ጊዜ ሲያገኝ ሊሰራ የሚችለውን ነገር ማሰብ በቂ ነው።

አሁን ደግሞ ስለ አጋጣሚዎች እናውራ። በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አውጋኝ እስኪ?

ቀድሜ እንዳልኩህ 2008 በጣም ደስ የሚል ዓመት ነበር። ታዲያ በዚሁ ዓመት ከደደቢት ጋር በመጀመሪያ ዙር ባደረግነው ጨዋታ ሦስት ለምንም ተረታን። የሚገርምህ እኛ ሁሉ ጎል አግብተን ብርሃኑ በእጁ የገባውን ኳስ አውጥቶት ነው የተረታነው። ይህ ጨዋታ ሁላችንንም አስቆጭቶን ነበር። ከዛ በሁለተኛ ዙር ከእነርሱ ጋር ስንጫወት በአሳማኝ ሁኔታ እኛም ሦስት ጎል አስቆጥረንባቸው አሸነፍናቸው። ይህንንም ጨዋታም በህይወቴ ምቼም አልረሳውም።

በተቃራኒውም የተከፋህበት አጋጣሚ ካለ በዚሁ ንገረኝ?

በጣም የተከፋሁበት አጋጣሚ ከጉዳት ጋር የተያያዘ ነው። ወልዲያ ከመውረዱ በፊት ከእነርሱ ጋር ስንጫወት በጣም ከባድ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። ይህ ክስተትም ከአዕምሮዬ የማይጠፋ መጥፎ ትዝታዬ ነው።

እርግጥ ገና ቢሆንም እግርኳስ ካቆምክ በኋላ በምን ሙያ ለመቀጠል ታስባለህ?

እርግኳስን መራቅ አልፈልግም። እስካሁንም ያለው ህይወቴ ከኳስ ጋር የተገናኘ ነው። ስለዚህ ኳስ መጫወት ካቆምኩ በኋላም በአሠልጣኝነት ሙያ ለመቀጠል አስባለሁ።

ምን አይነት አሠልጣኝ ነው መሆን የምትፈልገው?

ሁሉንም ጊዜው ሲደርስ እናየዋለን። እኔ አሁን በማስበው መንገድ ያኔ ተቀባይ ላላገኝ እችላለሁ። ስለዚህ በወቅቱ የሚፈጠረውን ነገር ተንተርሼ ሀሳቤን እቃኛለሁ።

ሽሪላ የሚል ቅፅል ሥም አለህ። ይህን ሥም ማነው ያወጣለህ? ለምንስ ተባልክ? ምን ማለትስ ነው?

ይህንን ሥም ያወጡልኝ በሠፈራችን ይገኙ የነበረ የእናቴ ጓደኛ ናቸው። አስታውሳለሁ ሐሙስ ቀን እኛ ቤት ተሰብስበው ዱኣ እያደረጉ እኔ በር ሳላንኳኳ ዘው ብዬ ወደ ገባሁ። ከዛ አሁን ያልኩህ ሴትዮ ‘ሽሪላ መጀን’ አሉ። ከዛ ይህ ተሰማ እና የሠፈር ልጆችም ሽሪላ እያሉ ይጠሩኝ ጀመር። እንግዲህ ከአምስት ዓመቴ ጀምሮ በዚህ ቅፅል ሥም መጠራት ጀመርኩ ማለት ነው። ሽሪላ ቁርአን ላይ ያለ የምስጋና ቃል ነው።

በእግርኳስ ውስጥ ከሚገኙ ግለሠቦች ያንተ የቅርብ ጓደኛህ ማነው?

ያው አብረውኝ ከተጫወቱት ተጫዋቾች ጋር ነው በደንብ የምቀራረበው። በተለይ መስዑድ የቅርብ ጓደኛዬ ነው። ከእርሱ በተጨማሪ ዳዊት እስቲፋኖስ፣ አቡበከር ናስር፣ ጀማል ጣሰው፣ ሀይደር ሸረፋ፣ እያሱ ታምሩ፣ አስራት ቱንጆ እና ሳልዓዲን በርጌቾ በእግርኳስ ውስጥ ያሉ የቅርብ ሰዎቼ ናቸው።

በስተመጨረሻ የቤተሰብ ህይወትህን በተመለከተ ሀሳብ ስጠኝ እና እናገባድ…

ሳሮን ሙሉጌታ የምትባል ምርጥ ሚስቴ ጋር ተጋብተን ኑሯችንን እየከወንን ነው። ከተጋባን አንድ ዓመት ተኩል ሆኖናል። እሷ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነች። እንደውም ዘንድሮ ነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምትመረቀው። በአጠቃላይ ደስ የሚል ህይወት ነው ከባለቤቴ ጋር እየመራሁ የምገኘው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!