የኒጀር አቻውን ነገ ምሽት 1 ሰዓት የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አመሻሽ ላይ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል፡፡
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋልያዎች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታቸውን ነገ ዓርብ ህዳር 4 በኒያሚው ስታድ ጀነራል ሴኒ ስታዲየም ከኒጀር ብሔራዊ ቡድን ጋር ሰባት ሺህ ተመልካቾች ብቻ በሚገኙበት ያከናውናል። የላይቤሪያ ዜግነት ባላቸው ዳኞች መሪነት የሚደረገውን ጨዋታው ለመከወን ሀያ ሶስት ተጫዋቾችን እንዲሁም በድምሩ ሰላሳ ስድስት የሚጠጉ የልዑካን ቡድንን በመያዝ ባለፈው ሰኞ ወደ ኒያሚ ያመራው ብሔራዊ ቡድኑ ያለፉትን ሁለት ቀናት ማረፊያውን ኑም በተባለ ሆቴል ካደረገ በኃላ ምቹ ባልሆነ የልምምድ ስፍራ ሲሰራ እንደነበር ከስፍራው ሲነገር የነበረ ሲሆን ለነገው ጨዋታ ግን ዛሬ ምሽት በእኛ ሰዓት አቆጣጠር 1 ሰዓት ሲል የመጨረሻ ልምምዳቸውን ለአንድ ሰአት ያህል ጨዋታው በሚደረግበት በስታድ ጀነራል ሴኒ አከናውነዋል፡፡
እስከ አሁን የቡድኑ አባላት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ መሆናቸው ሲገለፅ ለነገው ጨወታ ደግሞ ዛሬ ረፋድ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መደረጉ ተገልጿል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!