ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ የሰበታ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ለመሆን ከስምምነት ደርሷል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሳልፈው የሰጡት ሰበታ ከተማዎች በምትኩ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በውል መጠናቀቅ ምክንያት የተለያዩትን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን ለመቅጠር ከስምምነት መደረሱን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ምንዳ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
መስከረም 29 የአሰልጣኝ ቅጥር አውጥቶ ለመጨረሻ ስምንት አሰልጣኞችን ለቃል ፈተና ካስቀረ በኃላ የቅጥር ማስታወቂያውን በመተው ያለፉትን ሦስት ቀናት ከኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ጋር ያደረጉት ድርድር ወደ ስምምነት በመምጣቱ የፊታችን ዕሁድ ረፋድ ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው ዓለም ገና ከተማ ባለው ዓለም ሆቴል በይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓት የሚሾሙ ይሆናል፡፡
በረጅም ዓመታት የየመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቆይታቸው ብሔራዊ ቡድኑን ለኤዥያ ዋንጫ ካበቁ በኃላ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጥን ጥያቄን ተቀብለው ያለፉትን ሁለት ዓመታት ሲያሰለጥኑ የነበረ ሲሆን ከወራት በፊት መለየታቸው ይታወሳል፡፡ አሰልጣኙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እረፍት ለማድረግ እንዳሰቡ እና ለጊዜው ቡድን የመያዝ ሀሳብ እንደሌላቸው ገልጸው የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻም ከሰበታ ከተማ የቀረበላቸው ጥዬቄን ተቀብቸው ክለቡን ለመረከብ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!