ዋልያዎቹ በኒጀር ሽንፈት አስተናግደዋል

የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከ12 ወራት በኋላ መደረግ ሲጀምር ወደ ኒያሜ ያመራችው ኢትዮጵያ 1-0 ተሸንፋለች።

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመጀመርያ የነጥብ ጨዋታቸው በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ተክለማርያም ሻንቆን በግብ ጠባቂ ስፍራ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ያሬድ ባየህ፣ አስቻለው ታመነ እና ረመዳን የሱፍ በተከላካይ፣ መስዑድ መሐመድ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ሽመልስ በቀለ በአማካይ እንዲሁም አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ እና አቡበከር ናስር በአጥቂነት ተጠቅመዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ታፈሰ ሰለሞን እና ከነዓን ማርክነህ ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡ ተጫዋቾች ናቸው።

አንድ ሰዓት ላይ የጀመረው ጨዋታ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በ16ኛው ደቂቃ ሞንታሪ አዳሙ ከርቀት መትቶ በጎሉ አናት በወጣበት ሙከራ ኒጀሮች ለግብ ቀርበዋል። ከተከላካይ ጀርባ በሚላኩ ኳሶች እና አፈትልከው በመውጣት የጎል ዕድል ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ዋልያዎቹ የጨዋታውን መልክ ሊቀይሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን በቀላሉ ሲያመክኑ ታይተዋል። በ19ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ከርቀት ሞክሮ ኢላማውን ሲስት በ21ኛው ደቂቃ ጌታነህ ተከላካዮችን አምልጦ በመውጣት ያገኘውን እድል ግብ ጠባቂው ፈጥኖ በመውጣት አድኖበታል። በ22ኛው እና 26ኛው ደቂቃም መልካም አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ ቀይተዋል።

ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል እጅግ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ታይተውበታል። በተለይ በ39ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ከጎሉ ፊት ያገኘውን ነፃ ኳስ በአግባቡ ባለመምታቱ የጎል ቋሚው የመለሰበት እጅግ አስቆጪ እድል ነበር። በ41ኛው እና 45ኛው ደቂቃዎች ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ዩሱፍ አሊዩ በግንባር ገጭቶ አግዳሚ የመለሰበት እና በአናት የወጣበት ኳሶች በኒጀር በኩል በተመሳሳይ አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ።

ከመጀመርያው አጋማሽ ብዙም ያልተለየው ሁለተኛ አጋማሽ ጥቂት የጎል አጋጣሚዎች የተፈጠረበት ነበር። በፊት መስመሩ የነበረው ያለመናበብ ወደ ጎል እና ሙከራዎች የሚለወጡበት የተሻለ አጋጣሚዎች እንዳይጠቀሙ ያደረጋቸው ዋልያዎቹ በዚህ አጋማሽም ያገኟቸውን አጋጣሚዎች በቀላሉ አምክነዋቸዋል። ይልቁንም በ73ኛው ደቂቃ በጎል ክልል ውስጥ ኳስ አማኑኤል ዮሐንስ ኳስ እጅ መነካቱን ተከትሎ የፍፁም ቅጣት ምት ዩሱፍ አሊዩ ወደ ጎልነት ቀይሮ ኒጀርን መሪ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳሱን በመቆጣጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው በሙከራ ያልታጀበ ሆኖ የኒጀር መሪነት ወደ አሸናፊነት ሊሸጋገር ችሏል።

ኢትዮጵያ ሽንፈቱን ተከትሎ ከሦስት ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን የያዘች ሲሆን አራተኛም የምድብ ጨዋታዋን ባህር ዳር ላይ በመጪው ማክሰኞ ከኒጀር ታከናውናለች።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!