የዳኞች ገፅ | ተስፈኛው ፌደራል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ

በተለያዩ የሀገሪቱ የዲቪዚዮን ውድድሮች በጥሩ የዳኝነት ብቃቱ ይታወቃል። ወደ ፊትም ብዙ ተስፋ ከሚጣልባቸው ዳኞች መካከል የሚመደበው ወጣቱ ፌደራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የዛሬው የዳኞች ገፅ ዕንግዳችን ነው።

በምዕራብ ኦሮሚያ የተወለደው እና እንደብዙዎቹ ዳኞች አስቀድሞ በተለያዩ ክለቦች እግርኳስን ተጫውቶ በማለፉ ዳኝ ለመሆን መነሻ ሆኖታል። ጎን ለጎን ወደ ዳኝነቱ በመሳብም ከመምርሪያ የጀመረው ዳኝነት ህይወቱ እግርኳስን ካቆመ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን ወደ ዳኝነት በማድረግ ፌደራል ዳኛ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። በታችኛው የታዳጊ ዕርከን አንስቶ እስከ ከፍተኛ ሊግ የሚገኙ ውድድሮች ላይ ለዓመታት በከፍተኛ መሻሻል በትጋት እየሰራ ያለው ኤፍሬም ምንም እንኳን የሀገሪቱን ትልቁን ውድድር ፕሪሚየር ሊግ እስካሁን መምራት አይጀምር እንጂ የዳኞች ባለሙያ የሆኑት ኢንስትራክተሮች ወደ ፊት ትልቅ ዳኛ ሊሆን እንደሚችል ይመሰክሩለታል። ቀልጣፋ ፣ ፈጣን፣ በትኩረት እና በንቃት ሥራውን እንደሚሰራ በብዙ ሜዳዎች ያየነው ኤፍሬም ደበሌ በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን ጋብዘነዋል።

ትውልድ እና ዕድገትህ ?

የተወለድኩት ያደኩትም በሆለታ ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃም ሁለተኛ ደረጃም ትምህርቴን የተማርኩት እዛው ነው። በልጅነቴም እግርኳስን እየተጫወትኩ ያደኩት በዚህችሁ ከተማ በሆለታ ነው።

እግርኳስን በመጫወት በተለያዩ ክለቦች እንዳሳለፍክ ሰምቻለው እስኪ ስለ እሱ አጫውተኝ

አዎ በልጅነቴ በተወለድኩበት ሆለታ ከተማ በፕሮጀክት ታቅፌ እሰራ ነበር። በኃላም እዛው ሆለታ ውስጥ ለሆለታ ከተማ ተጫውቼ ለኦሮምያ ምርጥ ፣ ለሙገር እና ለተለያዩ ቡድኖች በጉዳት እግርኳስን እስካቆምኩበት ጊዜ ድረስ መጫወት ችያለሁ።

ወደ ዳኝነቱ ለመግባት መነሻ ምክንያትህ?

በስፖርቱ አሳልፌ ስለነበረ በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ወደ ዳኝነቱ እንድገባ ፍላጎቱ እና ተነሳሽነቱ ሊኖረኝ የቻለው። በካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ አማካኝነት ሆለታ ላይ የመጀመርያው የዳኝነት ኮርስ ሲሰጥ መውሰድ ቻልኩ። ይህን ኮርስ ወስጄ ግን ጎን ለጎን እግርኳስን በሥርዓቱ እጫወት ነበር። በ1998 ነፍሳቸውን ይማር እና በኢንስትራክተር መኮንን ለገሰ አማካኝነት ሁለተኛውን የዳኝነት የመምርያ ኮርስ ወሰድኩ ፤ ትምህርቴንም አላቆምኩም ነበር። ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ የኮንስትራክሽን ቴክሎኖጂ ማኔጅመት ኢንጅነሪንግ ከሁለት ዓመት በላይ ተምሬ ዊዝድሮ ሞልቼ ታምሜ ባቋርጠውም በዚሁ ዓመት ውስጥ በአልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በማነጅመት ዲግሬዬን ይዣለሁ።

ወደ ፌደራል ዳኝነት እንዴት አመራህ ?

በኢንስትራክተር አሰፋ ንጉሴ 2002 የፌደራል ዳኝነትን ኮርስ ወስጄ ውጤት እየጠበኩኝ ሳለ በመምርያ ደረጃ የወሰድኳቸው ሰነዶች በመጥፋታቸው ፌደራል ዳኛ መሆን እንደማልችል ተነገረኝ። በዚህ በጣም አዘንኩ ፤ እንዴት ይጠፋል ብዬ ዳኝነትን አልሰራም ብዬ ተስፋ የቆረጥኩበት ጊዜ ነበር። ለትምህርት ወደ ጅጅጋ ከመሄዴ በፊት በድጋሚ መውሰድ እንዳለብኝ ጋሽ ሠለሞን ገብረሥላሴ በጣም እየተቆጣ መከረኝ እንደገና ወደ ኃላ (እንደ አዲስ) መምርያ ኮርሶችን ወስጄ በ2006 ፌደራል ዳኛ ሆኛለው።

በፌደራል ዳኝነት የመጀመርያ ጨዋታህን ታስታውሰዋለህ ?

አዎ በሚገባ። የመጀመርያ ጨዋታዬን ለማጫወት የሄድኩት አዳዋ ከተማ ነበር። ያኔ ከፍተኛ ሊግ አልጀመረም ነበር። ውድድሩ ብሔራዊ ሊግ ይባል ነበር። አዳዋ ከደሴ ከተማ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ቦጋለ አበራ፣ ቃሲም አወል እና ከኮሚሽነር ጋሻው ረታ ጋር የመጀመርያ ጨዋታዬን አጫውቻለው። ከዚህ በኃላ በጣም ተደጋጋሚ የማጫወት ዕድል እየተሰጠኝ እዚህ ደርሻለው።

ያለፉትን ስድስት ዓመታት በፌደራል ዳኝነት ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውጪ ከታች በሚገኙ በሁሉም ውድድሮች ላይ ጥሩ አቋም ከሚያሳዩ ወደፊትም ተስፋ ከሚጣልባቸው አንዱ ነህ። እስካሁን በፕሪምየር ሊግ ለማጫወት ያልቻልክበት ምክንያት ምንድነው ?

በተለያዩ ዓመታት ወደ ፕሪምየር ሊግ እንደምገባ ሲነገረኝ ቆይቷል። ፕሪሚየር ሊግ እንግዲህ ፈጣሪ በፈቀደበት ሰዓት እገባለው ብዬ አስባለው። ዋናው ነገር ከእኔ የሚጠበቅብኝን ነገር ቀን በቀን ማድረግ ያለብኝን ልምምድም ሆነ ማንኛውም በህግ ዙርያ አዳዲስ ነገሮችን ራሴን እያዘጋጀው ትልቁን ህልሜን ለማሳካት ከፈጣሪ ጋር እጥራለው። ዕቅዴ ፕሪሚየር ሊግ ማጫወት ብቻ ሳይሆን እስከ ፊፋ ባጅ መለጠፍ ድረስ በመሆኑ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ሁሌም የተቻለኝን ጥረት አደርጋለሁ።

እስካሁን ባለው የታችኛው ዲቪዚዮን ውድድሮች ቆይታህ ያገኛሀቸው የምስጉን ዳኝነት ሽልማቶች አሉ ?

በ2007 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የፕሮጀክት ውድድር አዳማ ላይ ፣ በ2009 አርባምንጭ ላይ የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ የምስጉን ዳኝነት ክብርን አግኝቻለው። በተለያዩ ጊዜአት ደግሞ የሰርተፍኬት ሽልማትን አግኝቻለው።

በዳኝነት ህይወትህ አንተ ምሳሌ የምታደርገው ዳኛ አለ ?

ለኔ ሁሉም ዳኞች እኩል ናቸው። ሁሉም ምሳሌዎቼ ናቸው። እከሌ እከሌ ማለት አልችልም። ምክንያቱም ከኔ በላይ ካሉ ልምድ ካላቸው ዳኞችም ሆነ ከታችም ካሉት ዳኞች የሚያጫውቱትን ጨዋታ ባገኘሁት አጋጣሚ በሚገባ አያለው። ከእነርሱ የሚጠቅመኝን ግብአት እወስዳለው። ስለዚህ ሁሉም ዳኞች ለእኔ እኩል ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዳኝነት በአንተ እይታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?

ሁሉም ዳኞች የተለየ አቅም እንዳላቸው አስባለው። ዕድሉን ከማግኘት ካለማግኘት ጋር ተያይዞ ካልሆነ በቀር ኢትዮጵያ የዳኞች ሀብታም ናት። በዚህ በኩል ችግር የለም። ሆኖም እኛ ሀገር ካለው የእግርኳሱ አየር ጋር አብሮ አይሄድም። አየር ስልህ በክለቦቹ ውስጥ ካለው ጥሩ ያልሆነ ፍላጎት አንፃር ላንሆን እንችላለን። ለእነርሱ የማንመች መሆናችን የሚያሳድሩብን ተፅእኖ እንጂ በዳኝነት ከኢትዮጵያ ውጪ ካሉ ዳኞች ያለምንም ቴክሎኖጂ እገዛ በመተያየት፣ በመናበብ በራሳችን ቋንቋ በመግባባት ውድድሮችን እየመራን ነው ያለነው። በሀገራችን ምርጥ ኢንስትራክተሮች አሉ እነርሱ በሚገባ እያስተማሩ ብዙ አቅም ያላቸውን ዳኞች በየክልሉ እየፈጠሩ ነው። ስለዚህ በዚህ ዘመን ያለው የዳኝነት ሙያ በሁሉም ረገድ የተሻለ ነው ማለት የምችለቀው።

ገጠመኝ አለህ ?

አዎ ዳኛ ከሆንክ መቼም ገጠመኝ ይኖራል። 2011 ከፍተኛ ሊግ ሀላባ ከተማ ላይ ሀላባን ከመድን እያጫወትኩኝ 62 ደቂቃ ድረስ ጨዋታው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ሳለ ሀላባዎች ቴክኒካል ክስ ማስያዝ ይፈልጋሉ። እኔም በህጉ መሠረት ኮሚሽነሩን ፣ የሁለቱንም ቡኖች አምበሎች ጠርቼ እያነገርኩ ባለሁበት ሰዓት ከደጋፊዎች በተወረወረ ድንጋይ የተፈነከትኩበትን ቀን መቼም አልረሳውም። ጨዋታውን መቀጠል አልቻልኩም ፤ ወደ ሆስፒታል አመራሁኝ ጨዋታውም ለመቋረጥ ተገደደ። እውነት ለመናገር ፈርቼ ዳኝነትን ማቆም ካለብኝ በዚህ ጊዜ ነበር የማቆመው። ምንም ባላደረኩበት ሁኔታ ይህ መፈጠሩ መቼም አልረሳውም።

ራስህን በትልቅ ደረጃ ወደ ፊት ከፍ አድርገህ ለማጫወት ምን ታስባለህ ?

ቅድም እንዳልኩሁ ከእኔ የሚጠበቅብኝን እና ማሟላት ያለብኝን ነገሮች ለማድረግ መስራት እንዳለብኝ አስባለው። ከባለሙያዎች የማገኛቸው ተጨማሪ ዕውቀቶች ስላሉ በእነርሱ ላይ ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክሎኖጂ የተላዩ ትምህርቶችን እያወረድኩ በህግ ዙርያ በመውሰድ የሚገባኝን ትምህር እየወሰድኩ ነው። የአካል ብቃቴንም እንዴት ማስተካከል እንዳለብኝ ራሴን በየቀኑ በልምምድ በማዘጋጀት በቀጣይ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እሰራለው። በዓምላክ በተለያዩ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ላይ እንዴት የሀገሩን ስም ከፍ አድርጎ እንደሚያስጠራ የታወቀ ነው። ስለዚህ እርሱ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ። ይህም ብቻ አይደለም ከእርሱ አንድ ደረጃ ከፍ ለማለት አስባለሁ። በአሁን ሰዓት በዓምላክ የሁላችን ምሳሌ ነው። እርሱ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የማይመኝ ወጣት ዳኛ የለም።

አሁን እዚህ ለመድረስህ የምታመሰግነው አካል አለ ?

የዳኝነት ሰነዴ ጠፍቶ ዳኝነትን ለማቆም ተስፋ ቆርጬ ባለበት ሰዓት እንደ ሙያ አባት እንደ መምህር የማያቸው ኢኒስፔክተር ጌታቸው የማነህብርሀን ፣ ሻንበል ለማ ጉተማ ፣ ኢንስትራክተር ሠለሞን ገብረሥላሴ ለእነዚህ ሰዎች ትልቅ ክብር አለኝ ባለውለታዬ ናቸው። ብዙ ጓደኞቼ አብረውኝ አሉ። ለምሳሌ ሙስጠፋ መኪ ፣ አበራ አብርደው ሳዝንም ስከፋም በዳኝነቱ እንድቆይ አበረታተውኛል። ስለሆነም ከፈጣሪ በመቀጠል በጣም የማመሰግናቸው ሰዎች ናቸው።

የቤተሰብ ህይወት?

ትዳር መስርቼ መኖር ጀምሪያለሁ። እስካሁን ልጅ ባልወልድም በፈጣሪ ፍቃድ ወደፊት ተስፋ አደርጋለው።

በመጨረሻ መናገር የምትፈልገው ነገር ካለ ዕድሉን ልሰጥህ ?

ማናችንም ቢሆን በሙያ ውስጥ ያለን ሰዎች ለሙያችን ታማኝ ሆነን መስራት አለብን። ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ለሙያው የሚገባውን ክብር በመስጠት እና መስዋዕትነት በመክፈል ለሙያው ታማኝ መሆን አለብን እላለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!