የፕሪምየር ሊጉ የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ዛሬ ተከናውኗል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ2013 የሊጉን ጨዋታዎች መርሐ-ግብር በደማቅ ሥነ-ስርዓት ዛሬ ከሰዓት አውጥቷል።

ይጀመራል ተብሎ ከተነገረው 40 ደቂቃዎችን ዘግይቶ በተጀመረው በዚህ ሥነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እንዲሁም የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበሩት ሙሉጌታ ከበደ እና አሸናፊ በጋሻው ከክለብ ተወካዮች ጋር በመሆን በስፍራው ተገኝተዋል። በቅድሚያም የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በስፍራው የተገኙ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

“የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በብዙ ነገሮች ለየት ያለ ነው። ዛሬ የምናወጣውም ዕጣ አወጣት ከቀደሙት በብዙ ይለያል። ዋነናው ልዩነት ዲ ኤስ ቲቪ አብሮን መሆኑ ነው። አክሲዮን ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላ ሊጉን ሸጦ ነው የዘንድሮ ውድድር የሚደረገው። ክለቦች የሚያደረጉት ጨዋታም እንደ ቀደመው ጊዜ ስታዲየም በሚገባ ሰው ብቻ አደለም የሚታየው። ዲ ኤስ ቲቪ በሚገባበት ቦታ ሁሉ ይታያል። ስለዚህ ይህንን ዕድል ተሳታፊ ክለቦች በአግባቡ ለመጠቀም ጠንክራችሁ መጫወት እና ራሳችሁን መጥቀም አለባችሁ።

“ከዚህ በፊት እንደተባለው ዲ ኤስ ቲቪ ዘንድሮ በቀጥታ 4 ሚሊዮን ዶላር የሰጠናል። ከዛም በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በመጨረሻው ዓመት 5 ሚሊዮን ዶላር ይከፍለናል። በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ነገር ቢኖር እኛ ጠንክረን ከሰራን ከአምስት ዓመት በኋላ በዚህ መጠን ብቻ አንደራደርም። ስለዚህ ኩባንያው፣ ክለቦች በተለይ ደግሞ ተጫዋቾች ጠንክረን በመስራት ውጤታማ መሆን አለብን።” በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በመቀጠል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ ተከታዩን ሃሳብ በስፍራው ለተገኙ አጋርተዋል።

“ቁርጠኛ ሆነን የጀመርነው ሥራ ትልቅ ነገር ነው። ውጤቱንም እያየን ነው። ሲጀምር አሁን ላይ ውድድር እንደሚኖር አውቀን ዕጣ ለማውጣት መሰባሰባችን ትልቅ ነገር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሊጉንም ለዲ ኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ ተዘጋጅተናል። ከምንም በላይ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ግን የቤታችንን ገበና አደባባይ ይዘን ስለምንወጣ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ነው። ችግራችንን ትተን ነው ወደ ሜዳ መውጣት ያለብን። አለበለዚያ የዓለም መሳቂያ ነው የምንሆነው። ስለዚህ ሁላችንም የሚመለከተንን ስራ በአግባቡ መስራት አለብን። በመጨረሻ ይህ መልካም ነገር እንዲሳካ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። በተለይ ደግሞ የኩባንያው አመራሮች። ዲ ኤስ ቲቪም ተባባሪ ሆኖ ስለመጣ ማመስገን እፈልጋለሁ። መልካም የውድድር ዓመት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።” ብለዋል።

ከሁለቱ አመራሮች ንግግር በኋላ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወገኔ ዋልተንጉስ (ዶ/ር) የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱን አስመልክቶ ገለፃ ሲያደርጉ ተከታዩን ሀሳብ ብለዋል።

“የሀገራችን እግርኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሌሎች ዓለም ሰዎች ሊመለከቱት ነው። በዚህም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በፊት በፊት በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ሻምፒዮን ለመሆን አልያም ላለመውረድ ብቻ ነበር ውድድር የሚያደርጉት። ዘንድሮ ግን ሁሉም በየወጣበት ደረጃ ስለሆነ ሽልማት የሚሰጠው ጠንካራ ፍክክር ማድረግ አለበት። በዚህም ደግሞ ሊጉ ጥሩ ይሆናል ብለን እናምናል።

“ይህ እግርኳስ እዚህ የደረሰው በቀደምት ብርቅዬ እግርኳስ ተጫዋቾቻችን ነው። ስለዚህ የዛሬው የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት የቀድሞ ብርቅዬ ተጫዋቾቻችንን እውቅና እየሰጠን እናወጣዋለን።”

የመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር አዲስ አበባ፣ ጅማ እና ባህር ዳር ስታዲየሞች ላይ እንደሚደረግ ሲገለፅ የውድድሩ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብርም በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች በነበረው ሙሉጌታ ከበደ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች በነበረው አሸናፊ በጋሻው አማካኝነት ወጥቷል። በወጣው መርሐ-ግብር መሰረትም የሚከተሉት ቡድኖች በመጀመሪያ ሳምንት የሚገናኙ ናቸው።

የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱ ከተገባደደ በኋላ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ሁሉም የሊጉ ክለቦች የሴቶች እንዲሁም ከ23፣ ከ17 እና ከ15 ዓመት በታች ቡድኖችን እንዲይዙ መወሰኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ከ2008 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ከ20 ዓመት በታች የወንዶች ፕሪምየር ሊግ እንዲቀር ክለቦች መወሰናቸውም ተገልጿል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!