የነገውን የዋልያዎቹን የኒጀር ጨዋታ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል

ዛሬ ከቀጥር በኋላ ወሎ ሠፈር አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት የዋሊያዎቹን የአፍሪካ ዋንጫ የኒጀር ጨዋታ በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የዓርቡን የኒጀር ጨዋታ በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል።

“ከጉዞ ጀምሮ እዛ የነበረን ቆይታ መልካም ነበር። ሜዳም ላይ ቀድመን ባሰብነው መንገድ ነበር የተጫወትነው። እንደውም ከጠበኩት በላይ ነበር ተጫዋቾቹ የተጫወቱት። በግልፅ እራሱ ከጨዋታው በኋላ የቪዲዮ ትንተናው እና ቁጥሮች የሚያሳዩት ይህንን ነው። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ተጋጣሚ ጎል በመድረስ የተሻልን ነበርን። እንደውም 28 ጊዜ የኒጀሮች ግብ ክልል ደርሰናል። ግን ከጉጉት የመነጨ ይመስለኛል እድሎቹን አልተጠቀምንባቸውም። በአጠቃላይ ግን ከዛምቢያው የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ጀምሮ የቡድኑን እድገት በጣም ጥሩ ነው። ይህ ማለት ቡድኑ ክፍተቶች የሉበትም ማለት አደለም፣ ክፍተቶች አሉበት። እነሱንም ለመድፈን እንሞክራለን። ግን በፍላጎት፣ በመነሳሳት፣ በዝግጁነት እና ጨዋታን በመቆጣጠር ጥሩ ነበርን። ቢያንስ እንደውም በአርቡ ጨዋታ አቻ ይገባን ነበር።”

አሠልጣኙ የአርቡን ጨዋታ በተመለከተ ሃሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ካጋሩ በኋላ የነገውን የመልስ ጨዋታ ተንተርሰው ይህንን ብለዋል።

“ቀድሜ እንዳልኩት በአርቡ ጨዋታ ጥሩ ነበርን። ከኒጀር መልስ አራት ቀናት ነው ያሉን። በእነዚህም ቀናት ከበድ ያለ የሜዳ ላይ ሥራ መስራት አልቻልንም። ግን ተጫዋቾቹ በአርቡ ጨዋታ የሰሩት ነገር ጥሩ እንደሆነ እየነገርናቸው የአምሮ ሥራዎችን እየሰራን ነው። ክፍተቶችንም ለማስተካከል ጥረን ወደ ፉክክሩ ለመመለስ እንሞክራለን። የነገው ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ካሉት ጨዋታዎች ጥሩ ነጥቦችን መሰብሰብ አለብን።”

በመጨረሻም አሠልጣኙ ከአርቡ ሽንፈት በኋላ በተለያዩ አካላት ቡድኑ ላይ እየተሰነዘሩ ስላሉ “አላስፈላጊ ትችቶች” የተሰማቸውን ተናግረዋል።

“ይህ ብሔራዊ ቡድን የእኔ ብቻ ሳይሆን የሀገር ቡድን ነው። ስለዚህ ሰው ማሰብ ያለበት ብሔራዊ ቡድኑ የሀገር መሆኑን ነው። ሲጀምር በአርቡ ጨዋታ በተፈጠረው ነገር ፌዴሬሽኑ መጠየቅ የለበትም። እኔ ስለሆንኩ ተጫዋቾቹን መርጬ ወደ ሜዳ ያስገባሁት መጠየቅ ያለብኝ እኔ ነኝ። ግን በኒጀሩ ጨዋታ 7 ቢገባብን እንኳን ያለውን ነገር መገንዘብ አለብን። ስለዚህ ሁሉም ሰው በፊት የተፈጠረውን ነገር ትቶ በአንድነት ቡድኑን ማነሳሳት አለበት።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!