የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን የነገው ጨዋታ እንዴት ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም እንደተቀየረ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የዋልያዎቹን የኒጀር የደርሶ መልስ ጨዋታ በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት መግለጫ ተሰጥቷል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስለ ጨዋታዎቹ ሃሳባቸውን ከተናገሩ በኋላ የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ መጀመሪያ ባህር ዳር ላይ ሊደረግ የነበረውን ከዛም በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም የተዘዋወረውን የነገውን ጨዋታ በተመለከተ ተከታዩን ሃሳብ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል።
“ሰሞኑን በሀገራችን እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች በእግርኳሱም ላይ ተፅዕኖ እያደረጉ ነው። እንደሚታወቀው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ አራተኛ ጨዋታ ባህር ዳር ስታዲየም ላይ ሊደረግ ነበር። ፌዴሬሽናችንም ጨዋታው በመልካም ሁኔታ እንዲደረግ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ነበር። የኒጀር ልዑካንንም ሆነ የጨዋታውን ዳኞች የትራንስፖርት ወጪ ሸፍነን ትኬት ቆርጠን ጨዋታውን ስንጠባበቅ ነበር። ግን ከሰሞኑ ባህር ዳር ላይ በነበረው ነገር በረራዎቸ ቆሙ። እኛም ጨዋታውን በሌላ አማራጭ ለማከናወን ስንሞክር ነበር። ጨዋታውን ለማድረግም ሦስት አማራጮች ነበሩ። አንደኛው አማራጭ ጨዋታውን አዲስ አበባ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እዛው ኒጀር ላይ ጨዋታውን ማድረግ ነበር። በመጨረሻም በጎረቤት ሀገር ኬኒያ አልያም ግብፅ ጨዋታውን ማድረግ የሚል ነበር። እንደምታቁት ደግሞ በሀገራችን የባህር ዳር ስታዲየም ብቻ ነው ፍቃድ ያለው። ይህንን ችግር ለመቅረፈም ፌዴሬሽናችን በክቡር ፕሬዝዳንቱ አማካኝነት ከፍተኛ የስፖርት ዲፕሎማሲ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም እንደ አጋጣሚ የካፍ ፕሬዝዳንት ከሞሮኮ ወደ ማዳጋስካር ሲጓዙ ለሠዓታት በአዲስ አበባ እረፍት ሲያደርጉ ፕሬዝዳንታችን አግኝተዋቸው የተፈጠረውን ነገር አብራርተውላቸው ነበር። እሳቸውም ጉዳዩን ለካፍ ፀኃፊ እንዲሁም ለኒጀር እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እንድናስረዳቸው ነገሩን። ከዛም ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ለካፍ ይፋዊ ደብዳቤ ላክን። በመጨረሻም ካፍ በጊዜያዊነት የአዲስ አበባን ስታዲየም እንድንጠቀም ፈቀደልን።
“ሲጀምር እኛ ሁለት ጥያቄዎችን ነበር የጠየቅነው። አንደኛው ጨዋታው አዲስ አበባ እንዲሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 20% ደጋፊ በጨዋታው እንዲታደም ነበር። ግን ካፍ ከፀጥታ አንፃር እና ከስታዲየሙ ምቹነት አንፃር የደጋፊዎችን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ጨዋታው አዲስ አበባ እንዲካሄድ ብቻ ፈቀደልን።
“የጨዋታው የሴኩሪቲ ኦፊሰር ከዩጋንዳ ተመድቧል። ኦፊሰሩም ወደ ኒያሜ ያቀናው 36 ልዑካንን ጨምሮ ጥቂት የፌዴሬሽን ሰዎች በአጠቃላይ 5 ጋዜጠኞች እና 50 ሰዎች ብቻ ነበር ወደ ሜዳ እንዲገቡ የፈቀዱልን። ግን እኛ በዚህ ሳንስማማ ከካፍ ጋር በድጋሜ ተፃፅፈን ተጨማሪ ሰዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡ ሆኗል። በዚህም 50 ቪ አይ ፒ ሰዎች እንዲሁም 20 ጋዜጠኞች ብቻ ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተፈቅዷል።”
ፀኃፊው የመጫወቻ ሜዳው የተቀየረበትን መንገድ እና የነገውን ጨዋታ ለመመልከት ወደ ሜዳ የሚገቡ አካላትን በተመለከተ ገለፃ ካደረጉ በኋላ ጨዋታው በቴሌቪዥን ይተላለፋል ወይስ አይተላለፍም የሚለውን ጥያቄ በአጭሩ መልሰዋል።
“እንደሚታወቀው ይህንን ውድድር የፈረንሳይ ኩባንያ ነበር የሚያስተላልፈው። ከዚህ በፊትም ኩባንያው ከአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋር በመደራደር ነበር ጨዋታዎች በሃገራችን እንዲታዩ ሲሆን የነበረው። አሁን ግን ባለቀ ሰዓት የተፈጠሩት ነገሮች ብዙ ነገሮችን ለውጠዋል። ስለዚህ የነገው ጨዋታ በየትኛውም ቴሌቪዥን አይተላለፍም። የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይም ወስነን የወጣነው ነገር ይህንን ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!