ምጥን ምስክርነት ስለማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ – ከደብሮም ሐጎስ እና ገነነ መኩሪያ

በህይወት ከተለዩ ዛሬ 20 ዓመት የሆናቸው የቀድሞው አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታን ስብዕና በተመለከተ ከልጃቸው ደብሮም ሐጎስ እና ከጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ “ሊብሮ” ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

ኅዳር 07 ቀን 1993 ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን አሰልጣኝ ሀጎስ ደስታን አስመልክተው በሥራቸው ያለፉ ተጫዋቾች እና የሙያ አጋሮቻቸው ብዙ ይላሉ። ዘመናዊነት በተላበሰው የቡድን ግንባታቸው እና በአሰለጣጠን ሂደታቸው የሚሞገሱት ሀጎስን ለማሰብ በመጀመሪያ የመረጥነው ሀሳብ የግል ስብዕናቸውን ይመለከታል። ማስተር ቴክኒሺያን ሀጎስ በአየር ኃይል ፣ መድን እና መብራት ኃይል በነበራቸው ቆይታ በሰሯቸው ቡድኖች ውስጥ ከተጫዋቾቻቸው ጋር የነበራቸው ቅርርብ የተለየ እንደነበር ይነገራል። እንደሚታወቀው ለአሰልጣኞች ከተጫዋቾች ጋር የሚኖራቸው መልካም ግንኙነት ጥሩ ቡድንን ለመገንባት እና ከተጫዋቾች የሚፈልጉትን ትጋት ለማግኘት በእጅጉ ይረዳቸዋል። ይህን ማድረግ የቻለ አሰልጣኝ ደግሞ የወጣቶቹን ልብ ለማሸነፍ የሚረዳው የግል ባህሪው እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ይህን አስመልክተን ስለቀድሞው አሰልጣኝ የግል ስብዕና በጥቂቱ ለመረዳት ለልጃቸው ደብሮም እና ለጋዜጠኛ ገነነ ላቀረብነው ጥያቄ የሰጡን ምላሽም ሀሳቡን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

ደብሮም ሀጎስ

“ሀጎስን እንደአባት ለመግለፅ ሌሎች ቃላትን መጠቀም አይኖርብኝም። ፒያሳ የሚገኘው የወደብ ምግብ ቤት ባለቤት አቶ ክብረት የተናገሩት ነገር ሁሉን ነገር ይገልፃል ብዬ አስባለሁ። እሳቸው ምን ብለውኝ ነበር “ከእናንተ ጉሮሮ ላይ ነጥቆ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ያዋለ ሰው ነው” ብለው ነበር። እንደአባት የእኛ ብቻ ሳይሆን የሁሉም አባት ነበር። መልካም ሰው ነበር። ያለውን ሁሉ አካፍሎ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖርን የሚወድ ሰው ነበር። አሁን በእግርኳሳችን የጎደሉትን ነገሮች በእሱ ስብዕና ውስጥ ታገኛቸዋለህ። ቅንነቱ ፣ ለእግርኳሱ ያለው ታማኝነት ፣ ለሰዎች ያለው አክብሮት የተለየ ነበር። ሙያውን በጣም ነው የሚወደው ፤ አድሎ ያለው አሰራር በምንም ዓይነት አይመቸውም። ሁሌም ባመነበት ነገር ነው የሚጓዘው። የሌላው ሰው አካሄድ አያሳስበውም ፤ እሱ ግን ሥራው እንዳይበደል ማንኛውንም ነገር አሳልፎ ይሰጣል። ይሄንን ነገሩን በጣም ነው የምወድለት። ምሳሌ ሊሆን የሚችል ከሌሎች በተመሳሳይ በሙያው ካለፉ ሰዎች ጋር በመግባባት ለእግርኳሱ አስፈላጊውን ዕድገት ለማምጣት የለፋ ሰው ነው። ከዛም ውጪ በነበረው ስብዕና በሁሉም ዘንድ የሚወደድ እና የሚከበር ከፍተኛ የሆነ የሰው ፍቅር የነበረው ሰው ነው። በስራ ህይወቱ አብረውት ያሳለፉ ሰዎች ስለእሱ ምስክርነት ይሰጣሉ። መልካም ስራ ሰርቶ በማለፉም ሁሌም እኮራበታለሁ።”

ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ

“ከሜዳ ውጪ ባህሪው እንደአባት ወይ እንደጓደኛ ነው። በግል ባህሪው ከአሰልጣኞች ሁሉ ያማደንቀው እሱን ነው ፤ በጣም ተግባቢ ነው። ከሁሉም ተጫዋቾች ጋር ሰላማዊ ነበር። እንደአባት እንጂ እንደአሰልጣኝ አያዩትም። ሲያገኛቸው እንደጓደኛ ተቃቅፎ ስለቤተስብ እያወራ ነው ያምታገኘው። ተጫዋቾችን ሪፖርት አድርጎ ማስቀጣት ምናምን እሱ ጋር የለም። ድምፁን እንኳን ከፍ አድርጎ አይናገርም። በማህበራዊ ህይወቱ ጠንካራ ነበር ስንገናኝ ግን ምግብ ብዙም አይበላም ነበር ። ደብረዘይት ካልሄደ ብዙ ጊዜ ጓደኞቹ ጋር ነበር የሚያድረው።

“በአጨዋወት ረገድ ቴክኒካል ተጫዋቾችን ያስገባል ፤ አጨዋወቱ ወደፊት ነው። አጥቂዎቹን በደንብ ይጠቀማል። ጉልበተኛ አጥቂ እና ጉልበተኛ ተከላካይ ይፈልጋል። መሀል ሜዳ ላይ ከኳስ ጋር ጥሩ የሆኑ ተጫዋቾችን ይጠቀማል። እንደውም ገነነ የሚባል አጭር እና ደቃቃ ተጫዋች ነበረው፤ ያሰልፈው ነበር። ከአየር ኃይል እና መድን ይልቅ በመብራት ኃይል የሰራው ቡድን ጥሩ እግርኳስ ይጫወት ነበር።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!