የሊግ ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ስለ ዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ዕጣፈንታ ይናገራሉ

ከወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስመልክቶ ከሼር ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ጋር የተደረገ ቆይታ።

በትናንትናው ዘገባችን የዘንድሮ ዓመት የውድድር
ዘመን በተለይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚጀመርበት ቀን የሳምንታት እድሜ በቀረበት በአሁኑ ሰዓት ባሳለፍነው ቅዳሜ የሊግ ካምፓኒው የዕጣ ማውጣት ሥነስርዓት በማካሄድ ቡድኖቹ ተጋጣሚዎችን እንዲያውቁ አድርጓል። ከዚህ ባለፈ አሁን ባለው ሀገራዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሦስቱ የትግራይ ክለቦች በውድድሩ የመሳተፋቸው ነገር እንዴት ነው? ሊግ ካምፓኒው ከክለቦቹ ጋር የመረጃ ልውጥ እያደረገ ነው ወይ? እና ሌሎች ጥያቄዎችን አስመልክቶ ትናት ከሊግ ካፓኒው ሥራ አስኪያጅ ጋር ቆይታ አድርገን እንመጣለን ባልነው መሰረት ተከታዩን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።

” ባሳለፍነው ቅዳሜ በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት የሦስቱ ክለቦች ተወካዮች አጋጣሚ ሆኖ አልተገኙም። በመተዳደሪያ ደንባችን መሠረት ከ75% በላይ የሼር ካምፓኒው አባላት ከተገኙ ዕጣ ማውጣት እንደምንችል ደንቡ ስለሚፈቅድ ዕጣ የማውጣት ፕሮግራሙ ተካሂዷል። እስካሁን ሦስቱን ክለቦች ለማግኘት የምናደርገው ጥረት አልተሳካም። ሆኖም የሊግ ካምፓኒው እምነት እና ጥረት ሦስቱም ክለቦች እንዲሳተፉ ነው። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ሼር ካምፓኒው እየተወያየ፣ ጥረት እያደረገ ነው። ምክንያቱም ሦስቱም ክለቦች የሼር ካምፓኒው አባላቶች ስለሆኑ እና እኛ የምንፈልገው እንዲወዳደሩ ነው። ምክንያቱም እግርኳስ እና ፖለቲካ ምንም የሚያገናኝ ነገር የለም። ስለዚህ እነርሱን ማወዳደር ግዴታችን ነው። ከዚህ ውጭ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር በእኔ የኃላፊነት ደረጃ እንደዚህ ነው ብዬ መመለስ አልችልም።

” ወደፊት የኮሮና ቫይረስን መቆጣጠር ቢቻል እንኳ የዚህ ዓመት የውድድር ፎርማት በዝግ እንደሚካሄድ ነው ከውሳኔ የተደረሰው። በዚህም መሠረት ውድድሩ በፎርማቱ መሰረት በዝግ የምንጨርስ ይሆናል። ይህ በጠቅላላ ጉባዔ ተነጋግረን የወሰነው ነው። ምክንያቱም ፎርማቱን መቀየር በጣም ነው የሚያስቸግረው። በዝግ ጀምረን በኃላ ለተመልካች ክፍት የምናደርግ ከሆነ አንዱን ተጎጂ አንዱን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም የዚህ ዓመት ውድድሮች በዝግ የሚጠናቀቁ ይሆናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ