አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በይፋ ሰበታ ከተማን ተረከቡ

ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ሰበታ ከተማን በአንድ ዓመት የውል ስምምነት ዋና አሰልጣኝ በመሆን ዛሬ ተረክበዋል፡፡

ለረጅም አመታት የየመን ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ይዘው ለኢዥያ ዋንጫ ሀገሪቷን ካሳለፉ በኋላ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ተመርጠው ከ2011 ጀምሮ ዋልያዎቹን እስካለፈው ዓመት ሀምሌ ወር መርተው ፌዴሬሽኑ ውል ላለማራዘም በመወሰኑ ከብሔራዊ ቡድኑ የተለያዩት አሰልጣኙ ከሱዳኑ ኤልሜሪክ እንዲሁም ከታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ ክለቦች እንዲሁም ከሰበታ ከተማ የአሰልጥንልን ጥያቄ ጥሪ ቢደርሳቸውም እረፍት እንደሚፈልጉ ለሶከር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ገልጸው የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት በይፋ ክለቡን በአንድ ዓመት ውል ተረክበዋል፡፡

ዛሬ ዕሁድ ረፋድ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው አለምገና ከተማ ዓለም ሆቴል በነበረው ይፋዊ የቅጥር ሁኔታ የሰበታ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የመንግሥት እና የክለቡ አመራሮች በተገኙበት የቅጥሩ ሁኔታ ተፈፅሟል፡፡ በሥነ-ስርዓቱ ላይ አሰልጣኙ በይፋ በወር 120 ሺህ ብር እንደሚከፈላቸው የተገለፀ ሲሆን ለአንድ ዓመት በክለቡ እንደሚቆዩ ክለቡ ይፋ አድርጓል፡፡ አሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳሉት “ማረፍ እፈልግ ነበር። ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገር ክለቦችም ጥያቄ መጥቶልኝ ነበር። ግን የሰበታ ከተማዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ክለቡን ለአንድ ዓመት ብቻ ለማሰልጠን ተስማምቻለሁ። ባለኝ አጭር ጊዜም ቡድኑን ጥሩ ለማድረግ እሰራለሁ።” ሲል ተናግረዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!