የዲኤስቲቪ ባለሙያዎች ከክለቦች ጋር ውይይት እያደረጉ ሲሆን አዳዲስ መመሪያዎችም ቀርበዋል

የዲኤስቲቪ ባለሙያዎች ከሊግ ኩባንያው ጋር በጋራ በመሆን በብሮድካስት ደንብ አተገባበር ዙሪያ የክለብ የበላይ አመራሮችን እያወያየ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን ታህሳስ 3 ይጀመራል ተብሎ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ ሊጉ የኮቪድ 19 መመርያዎችን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ዙር ውድድሮችም በሦስት የሀገሪቱ ስታዲየሞች እንደሚከናወንም ከቀናት በፊት መገለፁ ይታወሳል፡፡ በሊግ ካምፓኒው የሚመራው የዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ውድድር ስያሜው ሆነ ቀጥታ ጨዋታዎቹን የማስተላለፍ መብቱን ዲኤስቲቪ ለአምስት ዓመት ስፖንሰር ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ዲኤስቲቪም መብቱን በመግዛቱ ክለቦች ሊያደርጓቸው የሚገቡ የተቋሙን መመሪያዎች በዛሬው ዕለት ከክለቦች ጋር እያደረገ በሚገኘው ውይይት ላይ አሳውቋል፡፡ በዛሬው ዕለት ከማለዳው ጀምሮ ቀኑን ሙሉ በሚቆየው በዛሬው የውይይት እና ስልጠና መርሀግብር ላይ ዐበይት ጉዳዮች ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

– የተጫዋቾች መለያ የቁጥር እና የስም አፃፃፍ ስታንዳርድ የተነሳ ሲሆን ክለቦችን ስፖንሰር ያደረጉ ድርጅቶች አርማቸውን በመለያዎች ላይ በምን መልኩ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ዲኤስቲቪ የራሱን መመሪያ በማቅረብ ክለቦች ተግባራዊ እንዲያደርጉት ወስኗል፡፡

– ክለቦች ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ሲመጡ ከጨዋታው መደርጊያ ሁለት ሰዓት ቀደም ብለው መገኘት እንዳለባቸው እና ተያያዥ የሆኑ የዲኤስቲቪን መመሪያዎች እንዲከተሉ፡፡

– ስፖንሰር ካደረገው ዲኤስቲቪ ውጪ የትኛው የሚዲያ ተቋም የፕሪምየር ሊጉን ጨዋታዎች በካሜራ መቅረፅ እንደማይችሉም የዲኤስቲቪ ተወካዮች ለክለቦች የገለፁ ሲሆን ይህን ጉዳይ የሚከታተል አንድ የሚዲያ ኦፊሰር በቀጣዮቹ ቀናት ለመቅጠር በሒደት ላይ መሆኑንም በውይይቱ ተነስቷል፡፡

– ሌላው የተነሳው ሀሳብ አስራ ስድስቱም የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የራሳቸው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያን ማዘጋጀት እና ክለቦችም በፍጥነት ሙያተኛ መመደብ እንዳለባቸውም ከውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ የሊግ ካምፓኒውም አፋጣኝ መረጃዎችን ለእግርኳሱ ማህበረሰብ ለማድረስ የህዝብ ግንኙነት ሥራውን በተለየ መልኩ ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም በውይይቱ ለክለቦች ተገልጿል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!