የትናንቱን የዋልያዎቹን ድል አስመልክቶ አስቻለው ታመነ ሀሳብ ሰጥቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለካሜሩኑ የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን እያከናወነ ይገኛል። በትላንትናው ዕለትም የምድቡ አራተኛ ጨዋታውን ከኒጀር ጋር አከናውኖ ሦስት ለምንም አሸንፏል። ይህንን ጨዋታ በተመለከተ ዛሬ ከቀጥር በኋላ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውንም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በቅድሚያ ከሰጡ በኋላ የቡድኑ ቀዳሚ አምበል (ጌታነህ ከበደ) ለህክምና ወደ ሆስፒታል መጓዙን ተከትሎ ሦስተኛው አምበል አስቻለው ታመነ ከጋዜጠኞች በተሰነዘሩለት ጥያቄዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ሃሳብ ሰጥቷል።

“የኒያሜው ውጤት ጨዋታውን የሚገልፅ አደለም። እኔ ከ2007 ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድን ተጫውቻለሁ። ግን እንደ ዓርቡን ያክል ተጋጣሚን አስጨንቀን ተጫውተን አናቅም። ግን ውጤቱ ለልፋታችን ምላሽ አልሰጠንም። ሲጀምር አሁን ያለውን ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ አስረስተን ሁሉንም የሀገራችን ህዝቦች አንድ ለማድረግ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ግን ይህ አልሆነም። ከጨዋታውም በኋላ በማኅበራዊ ገፆች ሲሰነዘሩ የነበሩ ነገሮች አዕምሮን የሚጎዱ ነበሩ። ግን አሠልጣኛችን ለውጤቱ እኔ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ ስላለን ብዙ አልተረበሽንም። ከዚሁ ጋር አያይዤ መግለፅ የምፈልገው ደጋፊዎች ውጤት ሲመጣ ብቻ ሳይሆን ውጤት ሲርቅም አብረውን መሆን አለባቸው።
“እንደምታቁት 7 ወር አርፈን ነው የተሰባሰብነው። ይህ በጣም ከባድ ነው። በዚህን ያክል ደረጃ አርፈን አናውቅም። ከዚህ ቀደም ቢበዛ አንድ ወር ነበር የምናርፈው። በዚህም የተወሰኑ ተጫዋቾች ኪሎ ጨምረው መተው ነበር። ግን በልምምዶች እና አብረውን በነበሩት የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች እርዳታ ወደ ቀድሞ አቋማቸው ተመልሰዋል።”
ለሚነሱለት ጥያቄዎች ምላሾችን በአጫጭር ዓረፍተ ነገሮች ሲመለስ የነበረው ተጫዋቹ በትላንቱ ጨዋታ ደጋፊዎች ወደ ስዲየም ገብተው ቢሆን ኖሮ የበለጠ ነገር ሊሰሩ እንደሚችሉ ተናግሯል። በመቀጠልም ተጫዋቹ ከያሬድ ባዬ ጋር “ገብቶበታል ስለተባለው እሰጣ ገባ” ይህንን ብሏል።
“በእኔ እና ያሬድ መካከል ምንም አልተፈጠረም። ‘አስቻለው እና ያሬድ ተኳርፈዋል’ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ፍፁም ውሸት ነው። ይህንን የተሳሳተ ፅሁፍ ለፃፈውም ሰው ገና ከአውሮፕላን ማረፊያ ሳንነሳ አብረን ሆነን ደውለንለት ጉዳዩን ጠይቀነው ነበር። ግን እርሱ ‘ከውስጥ ምንጭ ያገኘሁት ነው’ ብሎ መለሰልን። ይህ ግን ፍፁም ውሸት ነው። እኔ እና ያሬድ በክፉ እንኳን ተያይተን አናውቅም።”
አስቻለው በመጨረሻም ተጫዋቾችን ወክሎ ቡድኑ ያለውን ተስፋ በተመለከተ ሀሳቡን አጋርቷል።
“ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር የለም። ተስፋ አንቆርጥም። በሚኖረን ቀጣይ ጊዜ ተዘጋጅተን ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ እንሞክራለን።”
©ሶከር ኢትዮጵያ