​የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ልምምድ ማቆም እና የክለቡ ምላሽ…

የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከደመወዝ ጥያቄ ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ክለቡን ጠይቀው ምላሽ እንዳላገኙ በመግለፅ የዛሬ ልምምዳቸውን ማድረግ ሳይችሉ ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡

የጦና ንቦቹ ለ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በሶዶ ከተማ ከጀመሩ ሁለት ሳምንታት አልፏቸዋል፡፡ ቡድኑ የመጀመሪያዎቹን አንድ ሳምንታት በቀን ሁለቴ ልምምድ ሲሰሩ ከሰነበቱ በኃላ ያለፉትን አምስት ቀናት በቀን አንድ ጊዜ በአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ እና ረዳቶቹ እየተመሩ ልምምድ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ዛሬ ሀሙስ ከጠዋቱ 3:00 የክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከደመወዝ ጥያቄ ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘታችን ልምምድ ለማቆም ተገደናል በማለት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “ከሀምሌ ወር ጀምሮ ምንም አይነት ደመወዝ አልተከፈለንም። ይህው ኅዳር ሲመጣ አምስት ወር ሞልቶናል። እንዲከፈለን ለክለቡ በተደጋጋሚ ገልፀን መልስ አጥተናል። የዛሬ ሳምንት ካልተከፈለን እናቆማለን ብለን ስንወስን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ በቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ ወይንም ረቡዕ ደመወዛችሁን በሙሉ እንከፍላለን አሉን። ጠበቅን ግን አልተከፈለንም። በስራ አስኪያጁ በሰዓቱ ካልተከፈላችሁ ልምምድ አቁሙ እርግጠኛ ነኝ ይከፈላችዋል ብንባልም ሊከፈለን ስላልቻለ ልምምድ አቁመን ወደ የመጣንበት ሄደናል።” ሲሉ ጉዳዩን አብራርተዋል፡፡
ይህን የተጫዋቾቹን ቅሬታ ይዘን ለክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ እያሱ ነጋ ላቀረብነው ጥያቄ ተከታዩን መልስ ሰጥተውናል፡፡ “ተጫዋቾች ክለቡን ሊረዱ ይገባል። አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች አዳዲሶች ናቸው። ሆኖም ውላቸው በፌዴሬሽን አልፀደቀም። አንድ ክለብ ደመወዝ መክፈል ያለበት ደግሞ ውል ሲፀድቅ ነው። ይህን ከማድረግ አኳያ ክፍተት ተፈጥሯል። ካፀደቅን በኃላ እንከፍላለን ብለን ነበር ያሰብነው። ግን ድጋፍ የሚደረግልን ገንዘብ አልገባልንም። በቀጣይ ይገባል ብለን እየጠበቅን ነው። ይህን ቶሎ ለማስፈፀም እየተንቀሳቀስን ባለበት ሰዓት ነው ከእናንተ የተደወለልኝ። ደመወዝ በመክፈል ረገድ ቡድናችን የሚታማ አይደለም ። በትንሽ ምክንያቶች የተፈጠሩ እንጂ ላለመክፈል ብለን ያደረግነው አይደለም። ተጫዋቾችም መረዳት አለባቸው ካለው ወቅታዊ ጉዳይ አንፃር እንደ ክልልም የገንዘብ እጥረት አለ። ሌላ ገቢ የለንም የምናገኘው ከመንግሥት ነው። ከአሰልጣኞቹ ጋር ተገናኝቼ አውርቻለሁ። ልምምድ ማቆም ተገቢ አይደለም። አሁን ይሄን ችግር ለመቅረፍ እየጨረስን ነው። ወደ ልምምድም ሁሉም ተጫዋቾች መመለስ አለባቸው።” በማለት ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

በጉዳዩ ላይ አዳዲስ ጉዳዮች ካሉ ተከታትለን ወደ እናንተ የምናቀርብ ይሆናል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ